የሀገራት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ የምክክር ሂደት
ግንቦት 4/2017 ዓ.ም
የሌሎች ሀገራት የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ለሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ትምህርት ይሰጣሉ?
በተለያዩ ሀገራት የተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ለሀገራችን በጎ የሚሆን ትምህርትን አስቀምጠውልን እንዳለፉ የስነ-ምክክር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
የደቡብ አሜሪካዊቷ ኮሎምቢያ እ.አ.አ ከ2012-2016 ያካሄደችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በርካታ ተሞክሮዎች እንደተገኙበት ይነገራል፡፡
እንደ መዛግብቱ መረጃ ከሆነ ሂደቱ በዋነኝነት የግጭት እና የሀሳብ ልዩነቶች መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች ከስር መሰረታቸው በመለየቱ ረገድ አመርቂ ስራ ሰርቶ አልፏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሂደቱ ጠንካራ የሚባል የዜጎች ተሳትፎን አስተናግዶ መጠናቀቅ ችሏል፡፡
በሌላ በኩል በአህጉራችን አፍሪካ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ በታሪኳ ሁለት የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ያስተናገደች ሲሆን የሀገሪቱ ተሞክሮም ለኢትዮጵያ በበጎ መልኩ የሚወሰድ ነው፡፡ ኮዴሳ (Convention for a Democratic South Africa – CODESA) በመባል የሚታወቀውና እና እ.አ.አ ከ1991 እስከ 1993 የተካሄደው የምክክር ሂደት የመጀመሪያው የሀገሪቱ የምክክር እርምጃ ነው፡፡
የሂደቱ ዋነኛ ዓላማ የአፓርታይድ ስርዓትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማስወገድ ከዘር መድልዎ ነፃ የሆነች ሀገርን መፍጠር ነበር፡፡ በተጨማሪም ሂደቱ ሀገሪቱ በጊዜያዊነት የምትተዳደርበትን ሕገ-መንግስት የማዘጋጀትን ዓላማም አንግቦ ነበር፡፡ በሂደቱ እጅግ ብዙ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ በር ከፋች መሆን ችሏል፡፡
ሁለተኛውና በሀገሪቱ የተተገበረው የምክክር ሂደት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊዎች የነበሩበት የድርድር መድረክ Multiparty Negotiation Process – MPNP በመባል የሚታወቀው ነው ፡፡ ሂደቱ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1993 የተከናወነ ሲሆን ቀደም ሲል ተካሂዶ የነበረውን የምክክር ሂደት መሰረት አድርጎ የተነሳ ነበር፡፡ በዚህ እጅግ አመርቂ ውጤቶች በተመዘገቡበት ሂደት የሀገሪቱ ሀይሎች የተስማሙበትን ጊዜያዊ ሕገ-መንግስት በጋራ አፅድቀዋል፡፡
ታዲያ ኢትዮጵያ ከዚህኛው የምክክር ሂደት ምን ልትማር ትችላለች?

በደቡብ አፍሪካ በተደረጉት ሁለቱም የሀገራዊ ምክክር ምዕራፎች የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና የሀሳብ ውክልና በእጅጉ የደረጀ ነበር፡፡ ያ በመሆኑም ሀገሪቱ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የምትችልበትን ቁመና በአነሰ ጊዜ ለማምጣት አስችሏታል፡፡

በሀገሪቱ በተደረጉት ሁለቱም ሂደቶች ያለፉ የፖለቲካ ሀይሎች መግባባትን ዋነኛ ዓላማቸው አድርገው ወደ ሂደቱ በመግባታቸው ሁሉም በየበኩላቸው እጅግ ከባድ ሊባሉ የሚችሉ የመርህ እና የአቋም ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡ ይህም ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ ሌሎች ሀገራት ከሂደቱ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ትምህርት አስቀምጦ አልፏል፡፡
ለምሳሌ በሂደቱ ተሳታፊዎች በነበሩ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ጥቁሮች ያጡትን የመሬት ባለቤትነት ለማስመለስ እጅግ ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡ ሆኖም ግን በምክክሩ ሂደት ይህ አቋማቸው ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ በነጮች የተያዙ ይዞታዎች ሳይነኩ ለወደፊቱ ግን የመሬት አዋጅ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የደቡብ አፍሪካ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በሁለት ተከታታይ ዙሮች መካሄዱ በሂደቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ሚዛናዊ ውሳኔዎችን እና አካሄዶችን እንዲከተሉ በር ከፋች ነበር፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ጊዜ ለሂደቱ መሳካት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ሲሆን ባለድርሻ አካላትም በጊዜ ሂደት ነገሮችን በጥልቀት እና በሰከነ መንፈስ ለማየት ዕድሉን ያገኛሉ፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን ለዘመናት በቆየው የአፓርታይድ አገዛዝ እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች የውስጥ ሰላማቸውን አጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገሪቱ የምክክር ሂደቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ተዋናዮች ለሂደቱ መሳካት ያሳዩት ትዕግስት እና ፅናት ሂደቱን ውጤታማና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በመሆኑም በሀገራች ኢትዮጵያ ለሚደረገው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎች በርካታ ተሞክሮዎች መተግበራቸው ውጤታማ የምክክር ሂደት ለማድረግ የሚደረገውን ሂደት ይደግፋል፡፡ የሂደቱ ባለድርሻ አካላትም ከላይ የተጠቀሱትን ተሞክሮዎች በመቅሰም ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ይገባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!