የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በተጨመረው አንድ አመት በአማራና በትግራይ ክልሎች የምክክር ሂደቶችን ማጠናቀቅና ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማከናወን ተቀዳሚ ተግባራቶች ናቸው- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የካቲት 13/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሶስት ዓመታት አበይት ክንውኖችንና ቀጣይ የሥራ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ዛሬ የካቲት 13/2017 ዓ.ም ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

የኮሚሽኑን የሶስት አመት የስራ አፈፃፀምና የቀጣይ አንድ አመት የትኩረት ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ባለፉት ሶስት አመታት  የላቀ የማህበረሰብ ተሳትፎን መሠረት ያደረገ አካታች ሀገራዊ ምክክር ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ 1ሺ 230 ወረዳዎች በምክክር ሂደቱ መሳተፋቸውን ያብራሩት ዋና ኮሚሽነሩ በዚህም ከአሥር ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተደራጁ የአጀንዳ ሰነዶችን ኮሚሽኑ መረከቡን አስረድተዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በተለያዩ አህጉራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ጋር በበይነ መረብ አማካኝነት በመገናኘት ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ስራውን ሲሰራ በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመቀየስ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑንም ገልፀዋል፡፡

በተጨመረው የአንድ አመት ጊዜ በአማራና በትግራይ ክልሎች የምክክር ሂደቶችን አከናውኖ ማጠናቀቅና ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማከናወን ተቀዳሚ ተግባራቶቹ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡም “አንዳንድ ታጣቂ ቡድኖች እያነጋገሩን ነው፣ አሁንም በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፣ መምጣት ለሚፈልጉ ሁሉ ኮሚሽኑ አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል” ሲሉ በአፅኦት ተናግረዋል፡፡

ስለ ኮሚሽኑ ቀጣይ የአንድ አመት ስራ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው ከኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ካልገጠሙን በተጨመረው አንድ አመት የቀሩ ስራዎችን እናጠናቅቃለን ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከምክክሩ ሂደት ራሳችንን አግልለናል የሚሉ አካላት ሁሉ አሁንም ወደ ምክክር መድረኩ እንዲመጡም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው እየተካሄደ ያለውን ምክክር ሁሉም አልተሳተፉበትም በሚል ማጣጣል ተገቢ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምክክር ማድረግ የምትችሉበት ሁኔታ የለም በሚል ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ያከሉት ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በተደረገው ንግግር የምክክሩን አስፈላጊነት እንደሚያምኑበት ገልፀውልናል ሲሉ ቅቡልነቱን አረጋግጠዋል፡፡

እንደ አማራ ክልል ባሉ አካባቢዎች ምክክር ማድረግ ቅንጦት ነው በሚል ለተነሳው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው የአማራ ክልል አሁን ባለበት ሁኔታ ምክክር ማካሄድ ቅንጦት ሳይሆን የችግሩ የመፍትሄ አካል ሆኖ እንደመገኘት ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ወሳኝ ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ያስገነዘቡት ደግሞ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ናቸው፡፡ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር ለሁሉም ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ በመሆኑ ህዝቡ በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ አሳስበዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎችም ምክክሩ በተሳካ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ ተፋላሚ ሃይላትም ወደ ምክክሩ በመምጣት አጀንዳቸውን መስጠት መቻል እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡

መንግስት በአማራና በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ምክክር በተሻለ ሁኔታ መፈፀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበትም ነው ኮሚሽነር መላኩ ያስገነዘቡት፡፡

ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምክክሩ አካል ጉዳተኞችን ከማካተት አንፃር እየሰራ ስላለው ስራ በሰጡት ማብራሪያ ኮሚሽኑ አካል ጉዳተኞች በምክክሩ እንዲሳተፉ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የምክክር ቦታዎችን ምቹ ከማድረግ ረገድም ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ስራ መስራቱን አስገንዝበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኮሚሽኑ አንድ አመት መጨመሩን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር አንድ አመት የተጨመረው የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴ የሚከታተለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ክትትልና ግምገማ የምክክሩን ዓላማ ለማሳካት የቀሩ ወሳኝ ስራዎች በመኖራቸውና እነዚህ ስራዎች መሰራት ስላለባቸው ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኮሚሽኑ የሶስት ዓመታት አበይት ክንውኖችና የቀጣይ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ለማሳወቅ ዛሬ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል  በተዘጋጀው መድረክ በርካታ የሀገር ውስጥና ውጪ መገናኛ ብዙሃን ባሙያዎች ታድመዋል፡፡