ኮሚሸኑ የመረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋት ያለመ ውይይት አካሄደ
ጥር 6/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስለሥራ እንቅስቃሴዎቹ እና ስለ ምክክሩ ሂደት መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዘውን ውይይት ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የትራንስፖርት፣ የትምህርት እና የጤና ዘርፍ ተቋማት እና ማህበራት እንዲሁም ኢቲዮ ቴሌኮም ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
መድረኩ ከመገናኛ ብዙኃን አማራጮች በተጨማሪ ሕብረተሰቡ በሚገለገልባቸው ቦታዎች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የትራንስፖርት አማራጮች አማካኝነት ኮሚሽኑ ራሱን በሚያስተዋውቅበትና መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርግባቸው መንገዶች ዙሪያ ለመመካከር መዘጋጀቱ ተገልጧል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ሀገራዊ ምክክሩ ብቸኛው ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጫ መንገድ በመሆኑ በተቋማቸው አገልግሎቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ከኮሚሽኑ ጎን እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡
በርካታ ማህበረሰብ የሚገኝበት የትምህርቱ ዘርፍም የኮሚሽኑን መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥሩ አማራጭ መሆኑን የጠቆሙት የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባሉት አማራጮች ሁሉ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ለግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ሚናውን እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡
አንበሳ የከተማ አውቶቢስን ጨምሮ የተለያዩ የትራንስፖርት ዘርፍ ማህበራት እና ተቋማት በበኩላቸው የሰላም መረጋገጥ ለዘርፉ ብሎም ለሀገር የሚኖረውን ፋይዳ በመግለፅ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ይሳካ ዘንድ በግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ከኮሚሽኑ ጎን መሆናቸውን አበክረው ገልፀዋል፡፡
በርካታ ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞች ያሉት አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከብዝሃ መልዕክት ስርጭት እስከ ሞባይል አፕሊኬሽን ባሉት አማራጪች የኮሚሽኑን መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ሀላፊነት እንደሚወጣ ተቋሙን ወክለው የተገኙ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል፡፡
በጤናው ዘርፍም ባሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልቶች የኮሚሽኑን መልዕክቶች ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጤና ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በጋራ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በውይይቱ የተገኙ ተቋማት ለኮሚሽኑ መረጃዎች ተደራሽነት በየተቋሞቻቸው ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ተግባራትን ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የተለዩ ተግባራትን እየመራ የሚያስፈፅም ከሁሉም ተቋማት የተውጣጣ ግብረ-ኃይልም ተቋቁሞ ሥራዎችን መጀመር የሚያስችል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡





