የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በካናዳ የምክክር መድረክ የተሳተፉ ወኪሎች አጀንዳቸውን በውይይት አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረከቡ

canada participation
በካናዳ የምክክር መድረክ የተሳተፉ ወኪሎች አጀንዳቸውን በውይይት አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረከቡ
ጳጉሜ 2/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ወኪሎችን ለመምረጥ ትላንት ጳጉሜ 1/2017 ዓ.ም ወይም ሴፕቴምበር 6 በቶሮንቶ ያካሄደው መድረክ በስኬት ተጠናቋል፡፡
የምክክሩ ተሳታፊዎች በኮሚሽኑ እና በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ግልፅ ያልሆኑላቸውን ጉዳዮች በጥያቄና አስተያየት መልክ አንስተው በመድረኩ በተገኙ ኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በመድረኩ በሀገር ውስጥ በትግል ላይ የሚገኙ አካላትን እንወክላለን ያሉ ተሳታፊዎች ጭምር ጥያቄዎቻቸውን በግልፅ አቅርበዋል፡፡
አንዳንድ ተሳታፊዎች በተቃውሞ ስሜት ሀሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት ባቀረቡበት በዚህ መድረክ፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተሳታፊዎች ተቃውሞ ቢኖራቸውም በውይይቱ እንዲቀጥሉ በማድረግ የምክክር ሜዳን ሰፊነት አሳይተዋል፡፡
በተቃውሞ ድምፀት ለተነሱ ጥያቄዎችም በትዕግስትና በብስለት ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ከሁሉም ጎራ የመጡ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲመካከሩ አስችለዋል፡፡
ኮሚሽነሮቹ በኮሚሽኑ መርሆዎች መሰረት በትዕግስትና በብስለት የሁሉንም ሀሳብ አዳምጠው የተሳካ ምክክር እንዲካሄድ በማድረጋቸው ተቃውሞ ከነበራቸው ተሳታፊዎች ጭምር አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
ይህ ተግባራቸው ኮሚሽኑ የግልፅነት፣ አካታችነትና አሳታፊነት መርህን በአግባቡ እየተገበረ መሆኑን ያሳየ ስለመሆኑም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል፡፡
በኮሚሽሮቹ ምላሽና ማብራሪያ መግባባት ላይ የደረሱት ተሳታፊዎቹ በቡድን በቡድን በመሆን ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን አደራጅተው እና በሀገራዊ ጉባኤው የሚሳተፉ ወኪሎችን መርጠው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ማንኛውንም አይነት ሀሳብ እና ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በሆደ ሰፊነት በመመካከር፣ ለሀገራችን ችግሮች ፈውስ እናምጣ ሲሉ በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚሻገር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡