የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ የመወያያ አጀንዳዎች ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቀረቡ

endc human rights

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት፣ የሰብዓዊ መብትና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚመለከት ለመወያያ ይሆናሉ ያላቸውን አጀንዳዎች፣ ለኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቀረበ፡፡

ኅብረቱ ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የምክክር መድረክ፣  አጀንዳዎቹን ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተወካዮች ሲያቀርብ የኅብረቱ ኃላፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ የሚሆኑ የሰብዓዊ መብት አጀንዳዎችን በአራት በመክፈል፣  ከአሥራ አንዱ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች አንደኛው ለሆኑትና በመድረኩ ለተገኙት ወ/ሮ ብሌን ገብረ መድኅን አስረክቧል፡፡

የሰብዓዊ መብት አጀንዳዎች የህዳጣን መብቶችን፣ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርን፣ ተጠያቂነትን፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት የሚሠሩበትን ምኅዳር ላይ የሚያጠነጥኗቸው፡፡

የመሬት ባለቤትነት ላይ ጥርት ያለ መረጃ አለመኖር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በቅጡ አለማስተዳደር፣ ተጠያቂነት ደካማ መሆኑ፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት የሥነ ምኅዳር መጥበብና የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መስፋት አጀንዳዎቹን እንዲቀርጿቸው እንዳስገደዳቸው፣ በኅብረቱ ተጠባባቂ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ በሬሳ አበራ ለመድረኩ ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚመለከት አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች አሁንም ደኅንነታቸው ባልተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፣ የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልግ ስለሆነ፣ ውጤታማ የሆኑ የደኅንነት ሥራዎች አለመኖራቸው፣ እንዲሁም እውነተኛ ውይይቶችና ዕርቆች አለመኖራቸው ተፈናቃዮች ጉዳይ አጀንዳነት የሆነበትን ምክንያት አቶ በሬሳ አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽነር ብሌን በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በተለያዩ ቦታዎች ሥራዎቹን ከፋፍሎ እየሠራ ነው፡፡ አንደኛው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ እንደሆነ፣ በዚህም የሚሳተፉ አካላት በኮሚሽኑ ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሰብዓዊ መብቶችና በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራትን ኮሚሽኑ እያካተተ መሆኑን፣ በዚህ ሒደትም ሐሳቦችን ከሁሉም አካላት በማካተት እንደሚሠራ ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኮሚሽነሮቹ አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለን አይደለም አጀንዳዎችን የምናመጣው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው አጀንዳ የሚመጣባቸው ነገር ሕዝባዊ ውይይቶች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡን፣ ተቋማትንና መንግሥትን ወክለው ለምክክር የሚቀርቡ ተሳታፊዎችን ኮሚሽኑ እየለየ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡