ሥርዓተ-ፆታ ለምን የሀገራዊ ምክክር ሂደት አካል ሆነ?
የካቲት 9/2018 ዓ.ም
የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ማህበራዊ ዕሴቶች አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ የምክክር ሂደቱ ሕብረተሰቡ በሀገሩ ጉዳይ ትርጉም ያለው ተሳትፎን በማድረግ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖረው ለማስቻል ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ዕሴቶችን መጠቀሙ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ ሥርዓተ-ፆታ ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ግብዓት በመስጠት ለሂደቱ መጎልበት ጉልህ ሚናን ይጫወታል፡፡ ሥርዓተ-ፆታ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የሚገነባ ስርዓት ሲሆን ማሕበረሰቡ ለወንድ ወይም ሴት ፆታዎች የሚሰጠው ሚና፣ መገለጫ፣ ኃላፊነት፣ ዕድል፣ ወዘተ የሚደነገጉበት ነው፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ህዝቦች የሚያራምዷቸውን የሥርዓተ-ፆታ ሥርዓቶች እና ዕሳቤዎች መመርመር የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች እንዴት ከእነዚህ ዕሴቶች ግብዓት እንደሚያገኙ ለመመርመር ያግዛል፡፡ ከዚህ አኳያ የሚከተሉት ሀሳቦች ይህንን ለማብራራት ቀርበዋል፡፡
1. ሥርዓተ-ፆታ (Gender) የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንደሚስተዋለው የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ሊያሳኩ ከቆሙላቸው ዓላማዎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ መገለሎች እንዳይኖሩ ማድረግ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ መሆኑን የተለያዩ የሥነ-ምክክር ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በወንዶች ወይም ሴቶች ሊያዙ የሚገባቸውን የአመራር ሚናዎችን በመዳሰስ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በመተንተን እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ሚናዎችን ነቅሶ ከማከፋፈል እና ከመዘርዘር አንፃር ሥርዓተ-ፆታ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም ሥርዓተ-ፆታ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቶች መነሻ የምክክር አጀንዳን በማቅረብና ማህበረሰቡ ያለበትን እውነታ በመጠቆሙ ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ አለው፡፡
2. ሥርዓተ-ፆታ (Gender) ፖለቲካዊ ከዋኞችን ያሳያል
በሥርዓተ-ፆታ ላይ የተዘጋጁ የተለያዩ መዛግብት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ወንዶች ፖለቲካዊ ከዋኞች መሆናቸውን ሴቶች ደግሞ ማህበራዊ ከዋኝ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደትም ሴቶች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ማህበራዊ ከዋኝ እና ባለድርሻ አካል ከመሆን ባለፈ የሂደቱ ዐብይ ባለቤት በመሆን ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደትም የሥርዓተ-ፆታ አካታችነት የሴቶችን ተሳትፎ ከማሻሻል ጎን ለጎን ወንዶች በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዓውዶች ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና በምክክር እንዲሻሻል ያግዛል፡፡
3. ሥርዓተ-ፆታ (Gender) የሀገራዊ ምክክር ውጤት ላይ ተፅዕኖ አለው
የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ አድርገው ስለሀገራቸው መፃዒ ዕድል የሚመካከሩበት ሂደት ነው፡፡ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን አካታች የሆነ ሥርዓተ-ፆታን የተገበሩ ሀገራት የምክክር አጀንዳዎቻቸው ጥልቅ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ሂደቱም ቅቡል እንዲሆን የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይህም ለመፍትሔ ሀሳቦች ዘላቂነት እና ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈን የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከላይ የተዘረዘረውን እውነታ ከግንዛቤ በማስገባት በሀገራችን የሚስተዋለው የስርዓተ-ፆታ ሥርዓትን መሰረት አድርጎ ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎና ሚና ለማጎልበት እየሰራ ይገኛል፡፡





