ምክክር ከሌሎች የግጭት አፈታት ዘዴዎች የሚለይባቸው ባህሪያት
ጥር 12/2017 ዓ.ም
ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ ልምምድ እንደመሆኑ መጠን ፅንሰ ሀሳቡ ከሌሎች የሰላም ግንባታ ወይም ከግጭት አፈታት ዘዴዎች ጋር እየተቀላቀለ ብዥታን ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ ምክክር ኬሌሎች የግጭት አፈታት ዘዴዎች የሚለይበት የራሱ የሆኑ ተፈጥሮአዊ ባህሪያት አሉት።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የመጀመሪያው መገለጫ ሀገራዊ ምክክር የሶስተኛ ወገንን ጣልቃ ገብነት አስወግዶ የአንድ ሀገር ዜጎች የራሳቸውን ችግሮች ራሳቸው በመረጧቸው የሀገር ውስጥ ከዋኞች እና ተሳታፊዎች ማካሄድ መቻሉ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ሀገራዊ ምክክር ዘለግ ያለ ጊዜን የሚወስድ እና ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦች የሚመነጬበት ሂደት ሲሆን በስምምነት ላይ የተመረኮዙ ውሳኔዎችን እያስገኘ የሚሄድና በዜጎች መካከልም መተማመንን እያጎለበተ የሚዘልቅ ነው።
ይህ ሂደት አንኳር አንኳር የሆኑ አጀንዳዎችን ወደ መድረክ አምጥቶ የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቂ ጊዜ መውሰዱ ለውጤታማነቱ ትልቅ ሚና አለው።
በሶስተኛ ደረጃ የሀገራዊ ምክክር መገለጫ አካታችነት ሲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ዜጎችን በማሳተፍ በሂደቱ ባለቤትነት እንዲሰማቸው ያስችላል።
አካታችነት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና ባሰለድርሻ አካላት በማንነታቸው ወይም በመገለጫዎቻቸው ላይ በተመረኮዘ መንገድ ወደ ምክክር ከማምጣት በዘለለ የሀሳብ ብዘሀነትን የሚያስተናግድ ቁልፍ ተግባር ነው።
ከላይ የተገለፁት የሀገራዊ ምክክር ባህሪያት እንደተጠበቁ ሆነው ሂደቱ ከድርድር እና ከክርክር በምን እንደሚለይ የሚከተሉት ነጥቦች ያብራራሉ፡፡
- ሀገራዊ ምክክር እንደ ድርድር ዜጎች ሊያሳኩ በሚያስቧቸው ውስን የሆኑ ፍላጎቶች ላይ ስምምነቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ይልቅ ዜጎች ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን መደላድል ይፈጥራል፤
- ድርድር የሚታዩ ወይም የማይታዩ ይዞታዎችን በማከፋፈል ፣የራስ ጥቅምን በማስጠበቅ ፣ለአንደኛው ወገን በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ሙዓለ ንዋይን በመስጠት ግጭትን ለማብረድ የሚያገለግል ሂደት ነው፡፡ ምክክር ደግሞ የሰዎች ግንኙነትን እና ትብብርን በመገንባት በሰዎች መካከል የመከባባር፣ የመተማመን እና የመተሳሰብ ባህል በማዳባር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል፤
- በክርክር ውስጥ የሚዘወተረው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ የበላይነትን ለማሳየት ሲሆን በምክክር ሂደት ውስጥ ግን አንዱ የሌላውን ወገን ህመም በመስማት ለሌኛውም ወገን ችግር በጋራ መፍትሔን ለመፈለግ በጋራ ይሰራል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!