የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች እየታዩ ያሉ ተጓዳኝ ውጤቶች

የካቲት 10/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ ሀገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ግብ ለማሳካት በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ህዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ አጀንዳዎችን እያሳባሰበ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሰብሰብ ተቀዳሚ ግቡ መሆኑ ቢታወቅም ሂደቱ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን አይነት ቀጥተኛ ያልሆኑ በጎ አስተዋፅኦችን ለሀገር በማበርከት ላይ ነው፡፡

1. በዜጎች መካከል የተሻለ መተማመን እና ግንኙነትን ማዳበር

እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡ ውይይቶቹ በተለያየ ፈርጆች በተለዩ ወገኖቻችን መካከል መተማመንን በመገንባት ተስፋ ሰጪ የሆኑ በጋራ የመስራት ልምምዶች እንዲዳብሩ አስችለዋል፡፡

2. የባለቤትነት ስሜትን መፍጠር

የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው በምክክር ሂደቶቹ መሳተፋቸው እንዲሁም ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ማንሳታቸው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የኔነት ስሜት እንዲያዳብሩ እያስቻላቸው ይገኛል፡፡

3. የዲሞክራሲ ባህልን ማሳደግ

ሀገራዊ ምክክር ከተደረገባቸው አብዛኛዎቹ ሀገራት ማስተዋል የሚቻለው ሂደቱን አካታችና አሳታፊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይህም መሰረታዊ ከሆነው የዲሞክራሲ አስተምህሮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በመግለፅ፣ ወኪሎቻቸውን በመምረጥ፣ ውሳኔዎችን በመስጠት ብሎም በሂደቱ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው እንዳስቻለ መዛግብትም ያስረዳሉ፡፡

በዚሁ አግባብ በምክክር ሂደቶች ሲሳተፉ የቆዩ የባለድርሻ አካላት ወኪሎችም ከላይ የተጠቀሱትን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ የተገበሩ ሲሆን ይህም ዲሞክራሲን እንደ ባህል ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡

4. የመነጋገር ባህልን ማጎልበት

የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶችን ሀገር በቀል በሆኑ መንገዶች መፍታት የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓት ያልተፈቱ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ሂደቱ ሀሳቦች በሚገባ እንዲንሸራሸሩ መንገዱን አመቻችቷል፡፡ ይህም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ጎራዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ላይ ተወያይተው የመነጋገርን ባህል እንዲያጎለብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!