ኮሚሽኑ የሚያስመሰግን ተግባር እያከናወነ ነው- የአጋር ሀገራት አምባሳደሮች
ሀምሌ 16/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ከድጋፍ ሰጪ አጋር ሀገራትና ተቋማት ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ሀምሌ 14/2017 ዓ.ም ከሀገራዊ ምክክር ፕሮጀክት ቦርድ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት በእስካሁኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የአጋር ሀገራትን ድጋፍ በመገምገም በቀጣይ ተግባራት ላይ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ቦርዱ ለምክክር ሂደቱ መሳካት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ ድጋፎቹ ያስገኟቸውን ውጤቶችን በተመለከተም በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀጣይም አጋር አካላት ለምክክሩ ቀሪ ምዕራፎች ያላቸውን ሚና በመወጣት ከኮሚሽኑ ጋር የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ተጠሪ ሳሙኤል ዶኦ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነት እንደሚገነዘቡ ገልጸው፤ የተጀመረው የምክክር ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ቦርዱ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአጋር ሀገራት አምባሳደሮችም ኮሚሽኑ የሚያስመሰግን ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስታውቀው፤ ቀሪ የምክክር ምዕራፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ የየሀገራቸው መንግሥታት ለኮሚሽኑ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ቦርዱ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያን (ፕሮፌሰር) ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) አስተባባሪነት የአውሮፓ ሕብረትን፣ የኒውዝላንድ፣ የአየርላንድ፣ የሉግዘንበርግ፣ የኖርዌይን እና የጃፓንን መንግሥታት ያካተተ ነው፡፡ ሌሎች ሀገራትም በተለያዩ ጊዜያት አባል የሆኑበት ነው፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ከአሜሪካ ኤምባሲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዛካሪ ኔልሰን ጋር በተናጠል ተወያይተዋል፡፡
ትላንት ማክሰኞ ሀምሌ 15/2017 ዓ.ም በተደረገው ውይይት ኮሚሽኑ ከዳስፖራው ማህበረሰብ ጋር ለሚያደርገው የምክክር ምዕራፍ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግባቸው በሚችላቸው ጉዳዮች ላይ ከኃላፊው ጋር ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል፡፡
በውይይቱ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ ጋር የጀመራቸውን የአጋርነት መስኮች ከኃላፊው ጋርም ቀጥሎ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ንግግር ተደርጓል፡፡

