ኮሚሽኑ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ተረከበ
መስከረም 12/2017 ዓ.ም
ወደ ተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ያቀናው የኮሚሽኑ ልዑክ ከመላው የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከተወጣጡ የማህበረሰብ አባላት ጋር ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ በዱባይ ከተማ አካሂዷል፡፡
የምክክሩ ተሳታፊዎች በኮሚሽኑ እና በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ግልፅ ያልሆኑላቸውን ጉዳዮች በጥያቄና አስተያየት መልክ አንስተው በመድረኩ በተገኙ ኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚህ መድረክ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም ከሃይማኖት አባቶች ፣ ከሴቶች ማህበራት፣ ከልማት ማህበራት ፣ ከኮሚኒቲ ማህበራት፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከምሁራንና ተማሪዎች፣ ከንግድ ማህበረሰብ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ማህበራትና ተቋማት የተመረጡ ወኪሎች ተሳትፈዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች በቡድን ውይይት ያጠናቁሯቸውንና ያጀራጇቸውን አጀንዳዎች ለዋናው መድረክ አቅርበው አስተያየቶችን በማካተት ለኮሚሽኑ በይፋ አስረክበዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመወከል በኢትዮጵያ በቅርቡ በሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ወኪሎችንም መርጠዋል::
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኮሚሽነሮቹ ዱባይ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ ላሳዩት ድጋፍና አቀባበል እንዲሁም በምክክሩ ላደረጉት ንቁ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኮሚሽኑ የአሠራር ሥርዓት መሠረት በዚህ መድረክ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችም ከሌሎች አጀንዳዎች ጋር በኮሚሽኑ ምክር ቤት ተቀርፀው ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ግብዓት እንዲሆኑ የሚደረግ ይሆናል።

