Ethiopian National Dialogue Commission

በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው- ኮሚሽኑ

g11
በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው- ኮሚሽኑ
ሰኔ 27/2017 ዓ.ም
በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሠ በኮሚሽኑ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ በኮሚሽኑ አዳራሽ መግለጫ በሰጡበት መርሃግብር ነው፡፡
አቶ ጥበቡ በመግለጫቸው በትግራይ ክልል የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን፣ የዲያስፖራ የህብረተሰብ ክፍል አጀንዳ ለመሰብሰብ እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን እንዲሁም የአጀንዳ ቀረጻ እና የሀገራዊ ጉባኤ ዝግጅቶችንነ ሌሎች ወቅታዊ የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሂደቱን መጀመር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ ከክልሉ ጊዜያዊ ርዕስ መስተዳድር ጀነራል ታደሠ ወረደ ጋር በአካል ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የጀመረው ጥረት ተሳክቶ በክልሉ የምክክር ሂደቱ እንዲጀመር የፌደራል እና የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የምክክር ሂደቱን አካታችነት በተመለከተም ገለጻ ያደረጉት አቶ ጥበቡ፤ በምክክሩ ሲሳተፉ ቆይተው ካቋረጡ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ቃለ አቀባዩ በመግለጫቸው በሂደቱ እስካሁን ያልተሳተፉ ፓርዎች፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ኃይሎችን እና የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም በምክክር ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉም እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የታጠቁ ወገኖችንን ጨምሮ ሌሎች አካላት ሁሉ ወደ ምክክሩ መጥተው ይሳተፉ ዘንድ ሚዲያውን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ለማሳተፍ በበይነ መረብ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሉን የሚሏቸውን አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ድረ-ገጽና በኢሜይል በመላክ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
የዳያስፖራ የምክክር መድረኮች እንዲከናወኑ በኮሚሽኑ በኩል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
አቶ ጥበቡ አክለውም ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው የሚመራበት የአሠራር ሥርዐት ዝግጅት መደረጉንና አወያዮችን ለመምረጥ የሚያስችሉ መስፈርቶች ተዘጋጅተው ሰዎችን የማሰባሰብ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በመግለጫው የተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን አንስተው በቃል አቀባዩ በኩል ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡