2017 ዓ.ም ስኬታማ ስራዎች የተሰሩበት ዓመት ነው- ኮሚሽኑ
ጳጉሜ 5/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት እና የ2018 ዓ.ም ዕቅዶችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ በ2017 ዓ.ም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በርካታ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የሀገራዊ ጉባኤ ወኪሎች ምርጫ መድረኮች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
አጀንዳዎች በቀጥታ ከህብረተሰቡ መሰብሰባቸው እና ሀሳቦች በነፃነት መንሸራሸራቸው የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች መሆናቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በምክክሩ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂ ኃይሎችን ለማሳተፍ እንዲሁም በትግራይ ክልል የምክር ሂደት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ምክክር ውይይቶች በስፋት እየተከናወኑ ስለመሆናቸውም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የምክክር ሂደቱንና አስፈላጊነቱን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉም በመግለጫው ተብራርቷል፡፡
እነዚህ ተግባራት በአግባቡ ለመፈጸም ከተለያዩ አካላት ጋር በቅርበት ተሠርቷልም ብለዋል፡፡
በዐተቃላይ 2017 ዓ.ም ኮሚሽኑ ስኬታማ ስራዎችን ያከናወነበት ዓመት እንደነበር አቶ ጥበቡ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ከዳያስፖራ አጀንዳ ማሰባሰብና ተወካዮችን ማስመረጥ፣ ትግራይ ክልልን በምክክር ሂደቱ ማሳተፍ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በምክክር ሂደት ያልተሳተፉ ኃይሎችን ማሳተፍ፣ አጀንዳ መቅረጽ፣ ሀገራዊ ጉባኤ ማናወንና ምክረ ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት የማቅረብ ተግባራት እንደሚከናወኑም አቶ ጥበቡ ተናግረዋል፡፡





