የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ ለምን አስፈለገ?
ሀምሌ 15/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክሩ ባለድርሻ አካላት እንዲሆኑ ከለያቸው መካከል የዲያስፖራው ማህበረሰብ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለፅ እንደቆየው ኮሚሽኑ በቀጣይ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳ ይሰበስባል፡፡
በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለመሰብሰብ ኮሚሽኑ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በርካታ የበይነ-መረብ ውይይቶች ከመደረጋቸው በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ከሚኖሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ጋር በመገናኘት ገንቢ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
ሆኖም የዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በምን መልኩ አካታች እና ጠንካራ እንደሚያደርገው መጠየቁ ተገቢም ምክንያታዊም በመሆኑ ይህንኑ ለማብራራት የሚከተለው ቀርቧል።
1. የተለያዩ ልምዶችን እና ተሞክሮዎችን መቅሰም
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከሀገራቸው በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ወዘተ ምክንያቶች ርቀው እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን በሚኖሩባቸው የዓለማችን ክፍሎች ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን ብሎም አስተሳሰቦችን እንዲያጋሩ ሂደቱ በር በመክፈት አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይገመታል፡፡
2. በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ
ሀገራችን ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ እንዲሳተፍ ኮሚሽኑ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት የሁሉም ዜጎች በአግባቡ መሳተፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ባለቤትነታቸውን ከፍ ከማድረጉም በላይ በሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል፡፡
3. ዘላቂ የሆኑ የመግባባት መንገዶችን መቀየስ
በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን ዐበይት ጉዳዮች ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረኮች ማምጣታቸው የጋራ እና ዘላቂ የመፍትሔ ሀሳቦች ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!