የኮሚሽኑ የኮሚሽነሮች ልዑክ ከዳያስፖራ ኮሚዩኒቲ አባላት ጋር ተወያየ
መስከረም 29/2018 ዓ.ም
ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ እና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ የዳያስፖራ ተወካዮችን ለማስመረጥ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የኮሚሽነሮች ልዑካን ቡድን ከተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ተውካዮች፣ ከኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከኤምባሲው ሰራተኞች ጋር የቅድመ-ምክክር ውይይት አካሂዷል፡፡
የልዑክ ቡድኑ አባላት ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና የቀጣይ አቅጣጫዎቹን በተመለከተ ለኤምባሲው ሰራተኞች እና ለዳያስፖራ ማህበርሰብ አባላት ገለፃ አድርገዋል፡፡
በመጪው ቅዳሜ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 11 ቀን 2025 (ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም) በእንግሊዝና በአካባቢው አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች ለመለየት የውይይት መድረክ እንደሚያካሂድም ለአደረጃጀቶቹ አስገንዝቧል።
የዳያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች በቀጣይ ቅዳሜ የሚደረገውን የውይይት ሂደት አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽነሮች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መድረኩ ሀገራዊ ፋይዳቸው የላቀ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበትና የተሳካ እንዲሆን በአካባቢው የሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ኮሚሽኑን እንዲያግዙ ተጠይቋል።
አደረጃጀቶቹ እራሳቸው በምክክር መድረኩ በንቃት እንዲሳተፉና ሌሎች የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ስፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማስተባበር እንዲያግዙ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።





