የኮሚሽኑ ሰራተኞች በላቀ ተቋማዊ ተግባቦት ስራቸውን እንዲከውኑ ተጠየቀ
ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለተቋሙ ሠራተኞች ተቋማዊ አቅምን የሚያዳብር የሥልጠናና የውይይት መርሐግብር ባለፈው ቅዳሜ ሀምሌ 12/2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) “ተቋማዊ ተግባቦትና በቡድን የመሥራት ባሕል ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመነሻ ፅሁፍ የእያንዳንዱ የሥራ ተግባር መነሻና መድረሻ ተግባቦት (communication) እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም ስኬታማ ተቋማዊ ተግባቦት ኮሚሽኑ ከተለያዩ አካላት ጋር ለሚያደርጋቸው ግንኙነቶች መሠረት መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በበኩላቸው በእያንዳንዱ የሥራ እንቅስቃሴ የኮሚሽኑን ተልዕኮ ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ በሚከናወኑ የምክክር ሂደቶች ተናቦ የመሥራት ባህልን ማጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል።
በቀጣይ በሚኖሩ ሂደቶች በውይይት የተለዩ ግብአቶችን መሠረት በማድረግ በጋራ የኮሚሽኑን ዕቅድ ማሳካት እደሚገባ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው፡፡
ተቋማዊ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ ሠራተኞች እያከናወኑት ላለው የላቀ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ “የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ለሀገራዊ ምክክር” በሚል ርእስ በተጋባዥ የሃዋሳ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁራን ገለፃ ቀርቧል፡፡
ምሁራኑ ሚድያና ኮሙኒኬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት መሳካት የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመው በትኩረት እንዲሰራበት አስገንዝበዋል፡፡
የኮሚሽኑ የጥናትና ሥልጠና አስተባባሪ አቶ አንበሴ ፉራ “ተቋማዊ የእውቀት አስተዳደርና ሽግግር” በሚሉ ርእስ ባቀረቡት ፅሁፍ ለምክክሩ ስኬት በኮሚሽኑ ውስጥ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ባህል ሊዳብር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በሚድያ፣ ኮሙኒኬሽንና ተደራሽነተ ዘርፍ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ የተሳተፉ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ተቋማዊ አፈጻጸምን ማዳበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የቡድን ውይይት አድርገው የተደራጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለኮሚሽነሮች አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽነሮችም የሠራተኞችን ግብአት በመውሰድ ለቀጣይ ተቋማዊ ሥራዎች እንደሚጠቀሙባቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የኮሚሽኑን ተቋማዊ አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችና ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡





