የኮሚሽነር ዘገየ አስፋው የሕይወት ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው – 1934-2018 ዓ.ም (ግንቦት 4/2018 ዓ.ም)
የህይወት ታሪክ መዝገባቸው እንደሚያመለክተው ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በ1934 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ተወለዱ፡፡ ኮሚሽነሩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ከአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን አሜሪካ ከሚገኘው ከዊስኮንሲ ማዲሲን ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ሥራ ከጀመሩበት ዘመን ጀመሮ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሰሩ ሲሆን በተለይም በከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ የቀድሞዎቹ የመሬት አስተዳደር ሚኒስቴር፣ የግብርና እና የሰፈራ ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እና እንዲሁም የሥራ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት ካገለገሉባቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በ1967 ዓ.ም የወጣው የ ‘መሬት ላራሹ’ን አዋጅ በማርቀቅና በማስፈፀም ጉልህ ሚና እንደበራቸው በብዙዎች ዘንድ ይወሳል፡፡
ከሕግ ሙያቸው ባሻገር በተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራት የሚታወቁት ኮሚሽነር ዘገየ፣ ሁንዴ የሚባል ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ-ሰናይ ድርጅትን እና ቡሳ ጎንፋ የተባለ ማይክሮ ፋይናንስን በማቋቋም እና በመምራት በርካታ ግብረ ሰናይ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን የግል ማህደራቸው ያስረዳል፡፡ በዚህም የብዙዎችን ህይወት በመቀየር ጠንካራ የሚባል ሥራን ሰርተዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘገየ ከእነዚህ ሥራዎቻቸው ባሻገር ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ በተለይም የሰብዓዊ መብት አንቂ በመሆን በገጠሩ የሀገራችን ክፍል በሚኖሩ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝ፣ የሚሻሻልበትን መንገድ በመንደፍ እና ትምህርቶችን በማስተማር ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽነር ዘገየ በአካባቢ ጥበቃ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከአርሶ-አደሮች ጋር ለውጥን ሊያመጣ የሚችል ሥራ እንዲሰራ በማድረግ ፊት አውራሪ የነበሩ ሲሆን ይህም ተነሳሽነታቸው በአንዳንድ አካባቢዎች የአርሶ እና የአርብቶ አደሮችን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እንደነበረው ይወሳል፡፡
ኮሚሽነር ዘገየ ከየካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ግንቦት 3/2018 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት አገልግለዋል፡፡ ኮሚሽነር ዘገየ በኮሚሽኑ ውስጥ በአርአያነት፣ በታማኝነት፣ በትጋት እና በሀገር ፍቅር ስሜት ሥራቸውን በከፍተኛ የኃላፊነት ሥሜት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘገየ ባደረባቸው ህመም በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ትላንት ግንቦት 3/2018 ዓ.ም ምሽት 4፡30 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለኮሚሽኑ ማህበረሰብ መፅናናትን ይመኛል፡፡