የሃሳብ ልዩነቶችን ከማስተናገድ ያለፈ ሀገራዊ ምክክር
ህዳር 29/2018 ዓ.ም
የሃሳብ ብዝሃነት በሚስተዋልባቸው የዓማችን የተለያዩ ሕብረተሰቦች ምክክር እንደ መጀመሪያ አማራጭ ተደርጎ ሲወሰድ እምብዛም አይስተዋልም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ተሞክሮዎች አንደሚያሳዩት የሃሳብ ልዩነቶች ላይ ግልፅ፣ አካታች እና ተዓማኒነት ባላቸው መልኩ ውይይት ከተደረገባቸው የሀገርን ቁስል እና ሕመም የመሻር አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክርም ‘’ዜጎች ሲደማመጡ መተማመንን ያድሳሉ፤ ዜጎች ሲነጋገሩ ሰላምን ያወርዳሉ፤ ይህም ዜጎች በሀገራቸው ላይ የሚኖራቸውን የባለቤትነት መንፈስ ያደረጃል” በሚለው እሳቤ የተፈጠረ ዲሞክራሲያዊ ሂደት እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሀገራዊ ምክክር የሀሳብ ልዩነቶችን በማስተናገድ ሂደት ውስጥ ለሕብረተሰቡ ብሎም ለአንድ ሀገር የተለያዩ ገፀ-በረከቶችን ይዞ ይመጣል፡፡ የሚከተሉት ሀሳቦች ይህንን ያብራራሉ፡፡
👉ሀገራዊ ምክከር በማህበረሰቦች መካከል መተማመንን ይገነባል
የሀገራዊ ምክከር ሂደቶች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት (ባለደንታዎች) ባልተግባቡባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ፣ ስጋቶች እና ተስፋዎች ላይ በግልፅ እንዲነጋገሩ ዕድል ስለሚፈጥር ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥርጣሬዎችን በማስወገድ መተማመን እንዲደረጅ በር ይከፍታል፡፡
👉ሀገራዊ ምክክር የቅራኔዎችን መንስዔ ነቅሶ ያወጣል
ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በገጠሟቸው ቅራኔዎች ላይ ሲነጋገሩ የችግሮቹን ምልክቶች ብቻ ከማከም ይልቅ መንስዔዎችን በአግባቡ ለመለየት ይረዳል፡፡ ሂደቱ ዜጎች እንዲነገጋገሩ መፍቀዱ የተለያዩ ቁርሾዎችን በግልፅ እንዲያወጡና በሂደቱ ቁርሾዎችን ሊያባብሱ የቻሉ ትክክል ያልሆኑ መረዳቶችን በመለየት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡
👉ሀገራዊ ምክክር የሚመነጩ የመፍትሔ ሀሳቦች የጋራ እንዲሆኑ ያበረታታል
የሀገራዊ ምክክር መለያ ቀለም ዜጎች የሀገራቸው ሰላም፣ ፍትሕ እና አንድነት ላይ እኩል ድርሻ እና ባለቤትነት እንዳላቸው ማሳወቁ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሂደቱ የሚመነጩ የመፍትሔ ሀሳቦች ከበላይ አካል የሚመነጩ ሳይሆኑ በዜጎች የዳበረ ውይይት እና መግባባት ላይ ተመስርተው ይሆናል፡፡ ይህም ዜጎች በሂደቱ ላይ፣ ባመነጩት የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ብሎም በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡





