👉ባንመካከርስ?
የሀገራዊ ምክክር ተሳትፎ በፈቃደኝነት ወይስ በግዴታ?
የካቲት 7/2018 ዓ.ም
ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች፣ መንግስት፣ እና የማሕበረሰብ መሪዎች መካከል ለተፈጠሩ አለመግባባቶች በምክክር መፍትሔ ለማበጀት የሚካሄድ የዲሞክራሲ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ቅራኔዎች እና አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ ለማድረግ አበክሮ ይሰራል፡፡
ነገር ግን በዚህ ሂደት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ የሚቀርብላቸው ባለድርሻ አካላትና ተዋናዮች በሂደቱ የሚኖራቸው ተሳትፎ በፈቃደኝነት ይሁን በግዴታ መመርመሩ በሂደቱ ሊኖራቸው የሚገባውን መብትና ኃላፊነት እንዲገነዘቡ ይረዳል፡፡
👉በግዴታ የሚካሄድ ምክክር ፍሬ አያፈራም!
ሀገራዊ ምክክር በተፈጥሮው ሰብዓዊነትን በማስቀደም እና መተማመንን መሰረት በማድረግ የሌላውን ችግር ለመረዳት ቅን ልብ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሂደቱ እንደሌሎች አስተዳደራዊ ሂደቶች በተፃፉ ሕጋዊ ማዕቀፎች ከመንቀሳቀስ ይልቅ በሰው ልጆች እኩልነት በማመን ማንኛውም ዜጋ በግል እና በቡድን ለሀገሩ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋፅኦ አጉልቶ ለማሳየት ይሰራል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ አንዳንድ ሀገራት ተሞክሮ የሚያስተምረን ሂደቱ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ከሚያደርጉ ተጠቃሽ ምክንያቶች አንዱ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅ ማለትና ለሂደቱ ምቹ መደላድል አለመፈጠራቸው ነው፡፡
👉ምክክር ማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታች ነው!
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ተሳትፎ ማድረግ ግዴታ ባይሆንም በሂደቱ ከመሳተፍ መታቀብም የከፋ መዘዝ እና የታሪክ ተጠያቂነትን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ከምክክር መድረኮች ራሳቸውን ሲያገልሉ መፍትሔ ያልተገኘላቸው የሀገራችን አለመግባባቶች ተባብሰው ውድ ለሆነው የሰው ልጆች ሕይወት መጥፍት ምክንያት ሲሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ በመሆኑም የባለድርሻ አካላት በሂደቱ መሳተፍ ሀገራችን ዛሬ ላለችበት ቀውስ መፍትሔ ለማስገኘት ብሎም ነገ ለምትጓዝበት የመግባባትና የሰላም ጎዳና መስተካከል ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
👉👉ባንመካከርስ?
ከላይ እንደተገለፀውና በታሪክ አጋጣሚም ማየት እንደተቻለው ባለድርሻ አካላት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ለመሳተፍ ተነሳሽነታቸው ሲቀንስ የሂደቱ ውጤትም እንደሚፈለገው ላይሆን ይችላል፡፡ በዚህ አግባብ አለመመካከራችን ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩና የአለመግባባት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች እንዳይፈቱ እንቅፋት ይሆናል፡፡
👉ሀገራዊ ምክክርን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም
ሀገራዊ ምክክር በታሪክ አጋጣሚ የሚከሰትና ምንአልባትም ሌሎች ተቋማት ሊያስተናግዷቸው የማይችሏቸውን ጉዳዮች ለማስተናገድ የሚሰራ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክር ፦
• ላለመግባባት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች በባለድርሻ አካላት መካከል ግልፅ ውይይት እንዲደረግባቸው ያደረጋል፤
• ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቀውና አውዳሚ ከሆኑ ጦርነቶች ይልቅ በትንሽ ጊዜ እና ወጪ የመግባባትን መንገድ ይጠርጋል፤
• በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ባላተግባቡባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመደማመጥ መተማመንን እንዲያጎለብቱ ያስችላል፤
• ለዘመናት ለቆዩ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ችግሮች ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲመነጩ መደላድል ይፈጥራል፡፡
👉👉ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት!