የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የሀገራዊ ምክክር ሂደት በቀላል የሚገኝ እድል አይደለም፤ እንጠብቀው- ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ

for web

የሀገራዊ ምክክር ሂደት በቀላል የሚገኝ እድል አይደለም፤ እንጠብቀው- ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ
መስከረም 24/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሲዊዲን፣ በኖርዲክ ሀገራት እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተወካዮችን ለማስመረጥ ያዘጋጀው መድረክ በስቶክሆልም ከተማ ተጀምሯል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ ተሳታፊዎች የምክክር መድረኩ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚኖረውን ሚና በመረዳት ለመሳተፍ በመምጣታቸው በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሁሉም ህብረተሰብ እየተሳተፈበት ያለ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ይህንን በታሪክ ተደጋግሞ የማይገኝ አጋጣሚ እውን ለማድረግ በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ይህ ታሪካዊ እድል ለውጤት እንዲበቃ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን የአካታችነትና አሳታፊነት መርህን ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ምክክር እያካሄደ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ከትግራያ ክልል ውጪ 328 የምክክር መድረኮችን በማካሄድ አጀንዳዎችን ማሰባሰቡን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በትግራይ ክልልም ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በነዚህ ውይይቶች ሀገራችንን በፅኑ የዴሞክራሲ መሰረት ላይ ለመገንባትና የተረጋጋች ሀገር ለመፍጠር የሚያስችሉ አመላካች መፍትሄዎችን እየተመለከትን ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽኑ ስራውን በዚህ መልኩ እየሰራ ባለበት ሁኔታ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመሳተፍ ይልቅ ሂደቱን በዝምታ ማለፍ፣ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ሁኔታ በክልሉ ምክክር ለመጀመር አለማስቻሉ እንዲሁም የህዝቡ ፈጣን ውጤት መፈለግ እንደ ተግዳሮት የገጡሙት ጉዳዮች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በውጪ የሚኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል በሚል እምነት በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ እያደረገ ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ይህ በሲዊዲን ስቶክሆልም እየተካሄደ ያለው መድረክም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የዲያስፖራ ማህብረሰቡ በአገራዊ የልማት ፕሮጄክቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን በመጥቀስ አሁን ደግሞ ለአገራችን ዘላቂ ሰላም ቁልፍ በሆነው በአገራዊ ምክክር ላይ አጀንዳዎቻቸውን በነጻነት በመስጠት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት እንዲሁም በዚህ መድረክ ስለሚያከናውኑት ተግባር በኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ገለጻ ተደርጎላቸው ተሳታፊዎቹም በየቡድኑ ተከፋፍለው በመወያየት አጀንዳዎቻቸውን በማጠናቀር ላይ ይገኛሉ።