የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ወጣቶች የምክክር ሂደቱን በመደገፍ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

picture. haile
ወጣቶች የምክክር ሂደቱን በመደገፍ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
24/10/2017
“በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች የምክክር ሂደቱን በመደገፍ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የወጣቶች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር” በሚል መሪ ቃል የውይይት መርሐግብር አከናውኗል፡፡
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር ፐሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ ወጣቶች ሰላምን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
የወጣቶች ምክር ቤቶችን እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ጉልህ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡
ወጣቶች ለግጭት ተጋላጭ የሚያደርጓውን ጉዳዮች በምክክር መፍታት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን፤ ችግሮቻቸውን በምክክር ሲፈቱ ሀገርም፣ ትውልድም አትራፊ እንደሚኾኑ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የወጣቶችን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነር ብሌን፤ ወጣቶች በግልና በማኅበራት ደረጃ በምክክር ሂደቱ በስፋት መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በማኅበረሰብ ክፍሎች የምክክር ሂደት የወጣቶች ተሳትፎ ቢያንስ 20 በመቶ እንዲኾን መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ወጣቶች ከቀጥታ ውክልና ባሻገር በበጎ ፈቃደኛነትና በተለያዩ መንገዶች የምክክር ሂደቱን እየደገፉ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ወጣቶች ከኮሚሽኑ ጋር በቋሚነት የሚሠሩበት የማኅበራዊ ሚዲያ የግንኙነት ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ እንዲኖር እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት ወጣቶች ስለ ሰላምና ስለ ምክክር ያላቸውን አመለካከት እንዲያዳብሩ የማድረግ ተግባራት እንደሚከናወኑም ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድኅን አስታውቀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ከተለያዩ የወጣት መዋቅሮች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡