የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ጀመረ
ሐምሌ 25/ 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በበየነ መረብ አማካኝነት በአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡
ትላንት ሀምሌ 24/2017 ዓ.ም በበየነ መረብ አማካኝነት በተደረገው ውይይት ከግብፅ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬኒያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቦስትዋና እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረዓያ ኮሚሽኑ እስካሁን ሰላከናወናቸው ስራዎች እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የበየነ መረብ መድረኩ ዓላማ ከአፍሪካ ሀገራት ዲያስፖራ ማህበረሰብ አጀንዳ መቀበል እና በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጉባኤ ተሳታፊዎችን የሚመርጡ ኮሚቴዎችን ማደራጀት እንደሆነ ያብራሩት ደግሞ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን በቀጥታ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጉባኤ የሚወክሏቸውን ተወካዮች ስለሚመርጡበት ሂደት ሀሳብ እና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከተሳታፊዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኮሚሽኑ ከዳያስፓራው ማህበረሰብ በበየነ መረብ፣ በኢሜል እና በተመረጡ ሀገራት በአካል በመገኘት አጀንዳዎችን እንደሚያሰባስብ ተገልጧል፡፡
በቅርቡም ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ከዳያስፖራ አካላት ጋር በአካል ተወያይቶ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡
ኮሚሽኑ በተመረጡ የአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ኤዢያ ሀገራት በአካል በመገኘት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ አጀንዳዎችን እንደሚያሰባስብ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በየሃገራቱ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በጋራ በመደራጀት ለሀገራቸው የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን እያሰባሰቡ እንዲጠብቁም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡