ኮሚሽኑ ከአጋር አካላት ጋር ተወያየ
ነሐሴ 7/ 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት የአጋር አካላት ሚናን የገመገመበትና በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አጋር አካላት የወረዳ ተሳታፊዎችን ከመለየት ጀምሮ በአጠቃላይ ለኮሚሽኑ ስራ ስኬት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው አንስተው፣ ምስጋና አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) አጠቃላይ የኮሚሽኑን የስራ ክንውኖች የተመለከተ ገለፃ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በገለፃቸው በአጠቃላይ የምክክሩ ሂደት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በቀሪ የኮሚሽኑ ተግባራትም ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ከአጋር አካላት ጋር ቋሚ የውይይት መድረክ አለመዘርጋቱ፣ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ወጥነት አለመኖር በውይይቱ ላይ እንደ ክፍተት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
እነዚህን ክፍተቶች በቀጣይ አርሞ የተቀናጀ ስራ መስራት ይቻል ዘንድም ከኮሚሽኑና ከአጋር አካላቱ የተውጣጣ አስተባባሪ ቡድን ተቋቁሟል፡፡
ቡድኑ በቀጣይ ከትግራይ ክልል እና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ለማሰባሰብ በሚሰራው ስራ እንዲሁም በዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰራ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በዛሬው የአጋር አካላት መድረክ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት፣ የእድሮች ጥምረት፣ የመምህራን ማህበር፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ደስትኒ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ኢንክሉሲቭ ዲሎጉ እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡





