ኮሚሽኑ ከሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ጋር ተወያየ
ህዳር 14/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያና አፋር ክልሎች ከሚገኙ ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ በኦሮሚያ ክልል በአዳማና ጅማ ከተሞች በሁለት ክላስተር እየተካሄደ ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያን ችግሮች ከአፈሙዝ ይልቅ በውይይቱ የመፍታት ባህል እንዲሰርፅ ለማድረግ የወጣቶች፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው።
በሶስቱም መድረኮች ውይይቶቹን እየመሩ የሚገኙ ኮሚሽነሮች ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሚና የጎላ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች የግጭትና ጦርነት ገፈት ቀማሽ ከሆኑ አካላት መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸው በየመድረኮቹ ተነስቷል።
ከግጭት አዙሪት በመውጣት ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በተጀመረው ጉዞ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ሚናቸው የላቀ በመሆኑ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በአዳማና በጅማ ከተሞች እየተካሄዱ ባሉ መድረኮች ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የተወጣጡ የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ሀዳ ስንቄዎች ተሳትፈዋል።
በተመሳሳይ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ በክልሉ ከሚገኙ የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኛ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል።





