ኮሚሽኑ አሁንም በምክክሩ ያልተሳፉ አካላትን ለማሳተፍ ጥረት እንዲያደርግ የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ምሁራን ምክረ ሀሳብ አቀረቡ
ነሀሴ 15/2017 ዓ.ም (ባህርዳር)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ከነሀሴ 14-15/2017 ዓ.ም “ለውጤታማ የሀገራዊ ምክክር የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ በክልሉ ከሚገኙ 10 ዩኒቨርስቲዎች ከተወጣጡ ምሁራን ጋር ሲያካሂድ የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ ያለው ምክክር ከአካታችነትና አሳታፊነት አንፃር ያሉትን ጠንካራ አፈፃፀሞችና ክፍተቶች በተመለከተ ውይይቶች ተደርገው ለኮሚሽኑ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡
ኮሚሽኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጠ ዜጎችን በተለያዩ መሰረቶችና አደረጃጀቶች እያገኘ በማሳተፍ ምክክሩን እዚህ ደረጃ ማድረሱ የሚደነቅ ስራ መሆኑን ምሁራኑ አንስተዋል፡፡
ከአካታችነት እና አሳታፊነት አንፃር በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት፣ የህሊና እስረኞች፣ የፖለቲካ ስደተኞች እንዲሁም ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ወገኖችን እስካሁን በምክክሩ ሂደት አለማሳተፉ የውይይቱ ተሳታፊ ምሁራን እንደ ክፍተት ካነሷቸው ጉዳዮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አሁንም እነዚህ አካላት በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚሳተፉበትን አሰራር ኮሚሽኑ መዘርጋት እንዳለበት ነው ምሁራኑ በውይይታቸው እንደ ምክረሃሳብ የሰነዘሩት፡፡
ኮሚሽኑ ገለልተኛነቱን፣ ተዓማኒነቱንና ቅቡልነቱን ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ጉዳዮች እንዲጠነቀቅም ምሁራኑ በሰጡት ምክረሃሳብ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) በመርሃግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የመድረኩ ተሳታፊ ምሁራን ትኩረት ሰጥተው በመነጋገር ለሰጡት ምክረ ሃሳብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይም በሀገሪቱ ካሉ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር በቅርበት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ ከአካታችነት ጋር በተያያዘ ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፤ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት፣ የህሊና እሥረኞች፣ የፖለቲካ ስደተኞች እንዲሁም ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ወገኖች ሁሉ በምክክሩ ሂደት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡





