ኮሚሽኑ ተዓማኒትነት ለመገንባት የትኞቹን መንገዶች እየተከተለ ነው?
ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀጽ 3/1/ሐ ተዓማኒነት ከኮሚሽኑ መርሆዎቹ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ተዓማኒነት በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ሲታይ አንድ ወገን በሌላኛው ላይ (ግለሰብ ወይም ቡድን) ሊያሳድር የሚችለው በጎ የመታመን ደረጃን የሚገልጽ ነው፡፡
ዓለማችን በደረሰበት የቢሮክራሲ እና ቴክኖክራሲ አስተሳሰብ ተቋማት በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተዓማኒነት ከሚገነቡባቸው መንገዶች አንዱ ማህበረሰቡ ዕምነት ያሳደረባቸው ስርዓቶች ላይ ተመርኩዘው ስራዎችን ማከናወናቸው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በማህበረሰቡ ዘንድ አመኔታን ያተረፉ የተለያዩ አካላትን ማሳተፍ ለተቋማት ተዓማኒነት እና ስኬት ዓይነትኛውን ሚና ይጫወታል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በምክክር ሂደቱ ላይ ገለልተኛ ሚናን መጫወት ስለሚገባውና በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነትን መገንባቱ ለሂደቱ መሳካት አስፈላጊ ስለሆነ የሚከተሉትን ዐበይት ተግባራት ተዓማኒነትን ለማገንባት አከናውኗል/በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
👉ማህበረሰቡ ዕምነት ከሚጥልባቸው ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ማህበራት ጋር ለመስራት ስምምነቶችን በማድረግ ወደ ስራ መግባቱ፤
👉በሙያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በህዝብ ዘንድ ባለቸው ቅቡልነት እንዲሁም ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋፅኦ አንቱታን ያተረፉ አባላትን ያቀፈ የአማካሪ ኮሚቴ በማቋቋም እገዛን ለማግኘት መቻሉ፤
👉የሀገር በቀል የግጭት አፈታቶች ላይ ዋነኛ ከዋኞች የሆኑትን የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን የሂደቱ ተሳታፊዎች ማደረጉ፤
👉 የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን እና ተፅዕኖን ለመከላከል እጅግ ውስን በሆኑ የትብብር ማዕቀፎች ላይ ብቻ በጋራ ለመስራት መወሰኑ የሚሉት ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ በቀሪዎቹ የስራ ጊዜያት ዘመኑን የዋጁ አስተሳሰቦችን በአሰራር ስርዓቱ ላይ በማስረፅ ግልፀኝነትን እና ተዓማኒነትን ለማትረፍ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት!





