የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ገለጻ አደረገ

untitled design 20251209 183303 0000

ኮሚሽኑ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ገለጻ አደረገ

ህዳር 30/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች የእስካሁኑን የምክክር ሂደት እንዲሁም የቀጣይ ትኩረቶቹን በተመለከተ ዛሬ ህዳር 30/2018 ዓ.ም ገለጻ አደርጓል።

በገለጻ መርሀግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር አርአያ (ፕሮፌሰር) በመርሐግብሩ የተገኙ አምባሳደሮችንና የኤምባሲ ተወካዮችን በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ በአዲስ ማህበራዊ ውል ለማደስ ምክክር ያስፈልጋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በምክክሩ ሂደት የሁሉም ማህበረሰብ ድምጽ እንዲሰማ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ገለልተኛነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የኮሚሽኑ መርሆች መሆናቸውን አስታውሰው፤ ኮሚሽኑ በተለያዩ አካላት መካከል ያለውን ልዩነት ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ሀገራዊ መተማመን እንዲፈጠር ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን በማከናወን የተሟላ ምክክር ለማድረግ ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ጥረቶች እንደሚቀጥልም ዋና ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል፡፡

የምክክሩ መሳካት ለኢትዮጵያና ለቀጣናው ወሳኝ በመሆኑ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለሂደቱ መሳካት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)፤ የምክክሩን ሂደትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ምክክሩ ዘርፈ ብዙ ዘላቂ ሀገራዊ መፍትሔን እንደሚያመጣ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር መድረኮች ከቆዩ የልዩነት ጉዳዮች ይልቅ የወደፊት የመፍትሔ ሀሳቦች በስፋት እንዲንሸራሸሩ ዕድል ተፈጥሯል ሲሉም አክለዋል።

በሂደቱ የተረሱና እስከዛሬ ያልተሰሙ ድምጾች እንዲደመጡ መደረጉንም ኮሚሽነር አምባዬ አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምክክሩ አለመከናወኑ እና በሂደቱ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸውን በተግዳሮትነት ጠቅሰዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ የመጨረሻ መዳረሻ የዜጎች ህይወት በከንቱ የሚጠፋበት የፖለቲካ ሂደት እንዲቆም ነው ያሉት ኮሚሽነር አምባዬ፤ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የምክክር ሂደቱ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ዓላማውን እንዲያሳካ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ አምባሳደሮችና የኤምባሲ ተወካዮች የቀረቡትን ገለጻዎች መሠረት አድገው ጥያቄዎችን ሰንዝረው፤ በኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡