“ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሙያዊ ሥልጠናዎች ጠቃሚ ናቸ” ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም
ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም
ቤርጎፍ ፋውንዴሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በሥልጠናው መጀመሪያ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፤ ሥልጠናው ለኮሚሽኑ ስልታዊ ግቦች እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሥልጠናውን ያዘጋጁ አጋር አካላትን ያመሰገኑት ኮሚሽነሩ፤ በተለይም በቀጣይ ለሚዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ መሰል የምክክር ቴክኒካዊ ሥልጠናዎች በስፋት ያስፈልጋሉ ብለዋል።
የቤርጎፍ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሀንስ ጆአኪም ጌስማን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ፋውንዴሽኑ በርካታ የትብብር ሥራዎን ማከናወኑን አስታውቀዋል።
ለኮሚሽኑ አማካሪ ኮሚቴ የሚሰጠው ሥልጠናም በቀጣይ የሚከናወኑ የምክክር ምዕራፎችን በተመለከተ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚቀርብበት መኾኑንም አስረድተዋል።
ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚየቆየው የሥልጠና መድረክ መሠረታዊ የምክክር ጽንሰሀሳቦች፣ የተግባር ምዕራፎች አዘገጃጀት እና የሌሎች ሀገሮች የምክክር ልምድ በስፋት እንደሚዳሰስበትም ተገልጿል። የቡድን ውይይቶችና የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጦችም የሥልጠናው አካል እንደሚኾን ይጠበቃል።





