የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እስከአሁን ያከናወናቸውን እና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አቅርቧል፡፡
ግንቦት 8/2018 ዓ.ም
በቅርቡ በሞት ለተለዩት ለኮሚሽነር ዘገየ አስፋው የሕሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ውይይት የኮሚሽኑን ዐበይት ክንውኖችና እና እቅዶች በማቅረብ ቀጥሏል፡፡
ትላንት ግንቦት 7/2018 ዓ.ም የኮሚሽኑን ዐበይት የሥራ ክንውኖች በሪፖርት መልክ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በኮሚሽኑ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሔ መንገዶች እንዲሁም በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን እና የባለድርሻ አካላትን ሚና በተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ የቀረበውን ሪፖርት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መሳካት ያለውን ጠንካራ አቋም አረጋግጠዋል፡፡ በንግግራቸውም መንግስት ያልምንም ጣልቃ ገብነት ሂደቱን እንዲሳካ ጠንካራ አቋም እንዳለው ጠቁመው ከምክክሩ ሂደት የሚገኙ ምክረ-ሀሳቦችን ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ርዕሳነ-መስተዳደሮች፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ታዳሚዎች ሆነዋል፡፡





