“የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ
ህዳር 26/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
አጀንዳዎቹን የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች አመራሮች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አስረክበዋል።
በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ ከፓርቲዎች የተለያዩ አጀንዳዎችን መረከባቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ኮሚሽኑ ሲቋቋም ጀምሮ ሂደቱን እያገዘ መዝለቁን ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው የተደራጀ አጀንዳ በማስረከቡ በኮሚሽኑ ስም ያመሰገኑት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አጀንዳዎቹ ለሀገራዊ ጉባኤው በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም አረጋግጠዋል፡፡
የምክክር ሂደቱን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ኮሚሽነሩ ሂደቱ እንዲሳካ የፓርቲዎች ትብብር በቀጣይ ጊዜያትም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገራችንን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢዜማ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማገዝ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
ምክክሩ መሠረታዊና ዘላቂ የፖለቲካ ሥሪትን ብቻ የሚመለከት እንዲሆን በማሰብ አጀንዳዎቹ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኢዜማ በሁለት ከተማ አስተዳደሮችና በአስራ አንድ ክልሎች በተደረጉ የምክክር ምዕራፎች በስፋት መሳተፉ በመድረኩ ተገልጧል፡፡





