የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

“ትግራይ ክልልን ያላካተተ ምክክር ምሉዕ አይሆንም” ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕሮፌሰር)

t
“ትግራይ ክልልን ያላካተተ ምክክር ምሉዕ አይሆንም” ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕሮፌሰር)
ሀምሌ 23/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኮሚሽነሮች ልዑክ ትላንት ሀምሌ 22/2017 ዓ.ም ወደ መቐለ ተጉዞ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ካቢኔአቸው ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ የልኡካን ቡድኑ የጉዞ ዓላማ የትግራይን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ኮሚሽኑ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት እና የእስካሁን ሂደቶችን በተመለከተም ማብራሪያ የሰጡት ዋና ኮሚሽነሩ “ትግራይ ክልልን ያላካተተ ሀገራዊ ምክክር ምሉዕ አይደለም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ለግጭት የሚዳርጉ ምክንያቶችን በመለየትና ምክክር በማድረግ ሀገራዊ መግባባትን እንዲፈጠር በምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉንም አካላት በማካተት እየተከናወነ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል ያለበትን አውድ እንደሚረዳና ጦርነቱ ያስከተለውን ማህበራዊ ጉዳት እንደሚያሳዝናቸውም ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ ሀገራዊ ምክክርን ለመጀመር በቅድሚያ ከክልሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያደረግ ገልጸው፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚሽኑ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በማስተናገዱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት የሚያስመሰግኑ መሆናቸውን ጠቅስው፤ ኮሚሽኑ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንዳለው አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በትግራይ ክልል ስኬታማ እንዲሆን በክልሉ ያለውን የድህረ ጦርነት ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ መተማመን የሚፈጥሩ ተግባራትን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወደ ግጭትና አለመተማመን የሚወስዱ የሚዲያ ንግግሮችና ፕሮፓጋንዳዎች እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሌሎች በፌደራል መንግሥት በኩል ሊሟሉ ይገባቸዋል ያሏቸውንም ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የካቢኔ አባላትም ክልሉ ያለበትን ልዩ የድህረ ጦርነት ሁኔታ ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ምክክሩ በክልሉ እንዲጀመርና ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችም በስፋት አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያደርግ በመድረኩ ላይ ተገልጧል፡፡
የኮሚሽኑ ምክር ቤትም ግብዓቶችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሰባሰብ ከትግራይ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ምክክሩ ሊካሄድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ተገልጧል፡፡