የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ቤተ እምነቶች ያሏቸውን መልካም እሴቶች በመጠቀም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን እንዲደግፉ ተጠየቀ

dz
“ቤተ እምነቶች ያሏቸውን መልካም እሴቶች በመጠቀም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን እንዲደግፉ ተጠየቀ
መስከረም 7/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር የምክክር አስፈላጊነትን የተመለከተ የውይይት መድረክ ትላንት መስከረም 6/2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አከናውኗል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ፤ ኮሚሽኑ ሁሉም ሃይማኖቶች በምክክሩ ሂደት የሚሳተፉበትን አሰራር በስነዘዴው አካትቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
ለምክክሩ ስኬት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ በእስካሁኑ ሂደት የነበረውን የተቋማቱን ተሳትፎ በበጎ አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል በስተቀር በኹሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ መሰብሰቡን የገለጹት ኮሚሽነር ሙሉጌታ፤ ትግራይ ክልልንም በሂደቱ ለማካተት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በውጭ ሀገራትም ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክር መድረክ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቤተ እምነቶች ያሏቸውን መልካም እሴቶች በመጠቀም የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ሊደግፉ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመድረኩ የሀገራዊ ምክክር ፅንሰሀሳብ፣ የሀገራት ተሞክሮና የሃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ያላቸው ሚና እንዲሁም ያለፉት ሦስት ዓመታት የኮሚሽኑን የሥራ ሂደት የተመለከቱ ማብራሪያዎች በኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ቀርበዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎና ለምክክሩ ፍሬያማነት በቀጣይ ጊዜያት መወጣት ስለሚገባቸው ኃላፊነት የቡድን ውይይት በማድረግ ለመድረኩ ምክረሀሳቦቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በመድረኩ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር የሃይማኖት ተቋማቱ ለሰጧቸው ምክረሀሳቦች በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል።
የኮሚሽኑ ዓላማ ሀገራዊ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የምክክር ሂደቱን እንዲያግዝም ጠይቀዋል።
የምክክርን አስፈላጊነት በተመለከተ የሃይማኖት ተቋማት እንደ እምነቶቻቸው አስተምህሮ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዋል።