የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ባለመግባባታችን ባለን አኩሪ ታሪክ ልክ መራመድ አልቻልንም- ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ

542850819 795792089808889 445970687138209152 n
ባለመግባባታችን ባለን አኩሪ ታሪክ ልክ መራመድ አልቻልንም- ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ
ጳጉሜ 1/2017 ዓ.ም (ቶሮንቶ)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ ተጀምሯል።
መድረኩ በሀይማኖት አባቶች ፀሎት ነው የተጀመረው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ መድረኩን በከፈቱበት ንግግራቸው “እኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ የማይዘነጋቸው ድሎች ያስመዘገብን ነን” ብለዋል።
ከበርካታ 10 ዓመታት ወዲህ ግን የማንግባባና ግጭት የማያጣን መሆን መታወቂያችን ሆኗል ሲሉም አክለዋል።
በዚህ ምክንያት ካለን አኩሪ ታሪክ አንፃር በሚገባን ልክ ወደ ፊት መራመድ አልቻልንም ሲሉም ተደምጠዋል።
አለመግባባታችን በየጊዜው እየሰፋ አሁንም ድረስ የዘለቀ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ነን ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ሀገር የመቀጠላችንን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል ሲሉም ገልፀዋል።
አለመግባባቶቻችንን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ ሙከራዎቹ በሀይል አማራጮች ላይ የተወሰኑ ስለነበሩ ከኪሳራ የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም ብለዋል።
የሀይል አማራጮች አንዱን አሸናፊ፣ ሌላውን ተሸናፊ ከማድረግ የዘለለ ሁሉንም አሸናፊ ማድረግ የማይችሉ ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝ እዚህ ደርሰናል ሲሉም አክለዋል።
አሁን ግን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የምክክር መንገድ ተጀምሯል፤ ይህንንም ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ሲሉም ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮችን በህዝባዊ ውይይት በመለየት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ገለፃ ይህ ሂደት ህብረተሰቡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲወስን ያስቻለ ነው።
ይህንንም ለማጠናከር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካኝት በምክክሩ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ሂደት በርካታ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ዳያስፓራው በሀገሩ ጉዳይ የሚወስንበት እድል እንዲያገኝ ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ በካናዳ እየተካሄደ ያለው መድረክም የዚህ ጥረት አካል መሆኑንም ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ በንግግራቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።