በካናዳ የምክክር መድረክ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ገቢ ተደረጉ
መስከረም 6/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጳጉሜ 1/2017 ዓ.ም በቶሮንቶ ከተማ አጀንዳ ማሰባሰቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ መድረክ የተሰበሰቡ ባለ 66 ገፅ 11 የአጀንዳ ሰነዶችን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ በኮሚሽኑ ዶክመንቴሽን መምሪያ በኩል ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ገቢ አድርገዋል፡፡
አጀንዳዎቹ በ11 የግለሰቦች፣ የተቋማትና ማህበራት ቡድኖች ተደራጅተውና ተጠናቅረው የቀረቡ ናቸው፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 22 ግለሰቦች በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 25 የቢዝነስ ሰዎች(ነጋዴዎች) በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 8 የሲቪል ማህበረሰብ ግለሰቦች በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 25 ግለሰቦች በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 7 ግለሰቦች በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 27 የሃይማኖት ሰዎች በአንድ ቡድን፣ በካናዳ ነዋሪ የሆኑ 6 የሚድያ ባለሙያዎች በአንድ ቡድን በመሆን አጀንዳዎቻቸውን አደራጅተው አስረክበዋል፡፡
በተጨማሪም የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት በቶሮንቶ ፣ በኦቶዋና አካባቢው የኢትዮጵያዊያን ካናዳዊያን ሙስሊም ማህበር እንዲሁም የኦሮሞ ሄሪቴጅ ማህበር በተቋም እና በማህበር ደረጃ አጀንዳዎቻቸውን አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
በካናዳ የሚገኙ 6 ምሁራንም አጀንዳዎቻቸውን በአንድ ቡድን በማጠናቀርና በማደራጀት ለኮሚሽኑ ካቀረቡ አካላት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኮሚሽኑ የአሠራር ሥርዓት መሠረት አጀንዳዎቹ ከሌሎች አጀንዳዎች ጋር በኮሚሽኑ ምክር ቤት ተቀርፀው ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡





