የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

“በኦሮሚያ ክልል የምክክር ሂደት የህብረተሰቡ የመደማመጥና የመወያየት ፍላጎት የሚደነቅ ነው” – ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)
ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም
ካለፈው ሰኞ ታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የህብረተሰብ ክፍሎች የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
የህብረተሰብ ክፍሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁን አስመልክቶ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) እና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለጋዜጠኞች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በኦሮሚያ ክልል የምክክር ሂደት የህብረተሰቡ የመደማመጥና የመወያየት ፍላጎት የሚደነቅ ነው ሲሉ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በምክክሩ ሂደት ሁሉም ድምፆች ሲደመጡ፣ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ሲያዳምጥ ተመልክተናል፣ ይህም ምክክሩ ያዳበረው የዴሞክራሲ ባህል ነው ሲሉም አክለዋል።
በምክክሩ ሂደት ጠለቅ ያሉ የአጀንዳ ግብአቶች ተነስተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ አጀንዳዎች መቅረባቸውንም ተናግረዋል።
ተወካዮች ሲመረጡ በግልጽና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መከናወኑ ትልቅ ትምህርት መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ከሎጂስቲክስ አኳያም ከ7ሺ በላይ ተሳታፊዎች ከመላው ኦሮሚያ ተጓጉዘው አዳማ መገኘታቸውና መስተናገዳቸው ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም አክለዋል።
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምክክር ማድረጋቸው ለሌሎች ክልሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ ለመግባባት፣ ለመተማመን እና ምክክርን ባህል ለማድረግ ተግባራዊ ትምህርት እንደተገኘበትም አብራርተዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለምክክሩ ሂደት እያደረጉ ላሉት አስተዋፅኦም አመስግነዋል።
መድረኩ እንደ ሀገር ተስፋ እንድንይዝ የሚያደርግ ነው ሲሉም ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በመግለጫው ላይ አንስተዋል።