የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

“በእስካሁኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት ሚና የላቀ ነው” – ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ

ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳዎችን አስመልክቶ ከሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት ጋር የግብአት ማሰባሰቢያ ውይይት እያከናወነ ነው።

በውይይቱ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ዋና ዋና የኮሚሽኑ ክንውኖችና የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም የተቋማትና ማኅበራት ሚናን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ከወረዳ ጀምሮ የነበረው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የምክክሩ ሁሉን አካታችነት አመላካች ነው ብለዋል።

የረዥም ዘመናት የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች እንዲፈቱ የሚያስችሉ መሠረታዊ የምክክር ምዕራፎች መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡ ምክክሩን በባለቤትነት ስሜት በመያዝ ለሂደቱ ሚናውን ሲወጣ እንደቆየ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ሁሉንም የሀገራችንን ወረዳዎች ለማሳተፍ ታቅዶ 93% አፈጻጸም እንደተመዘገበም አስረድተዋል።

በዚህ ሂደት የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት ሚና ጉልህ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመወከል ንግግር ያደረጉት የሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝደንት አቶ አሕመድ ሑሴን ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በፖለቲካዊ መድረክ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ባሳተፈ ሰላማዊ ውይይት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሲቪክ ማኅበራት ለምክክሩ ስኬታማነት በቀጣይም ሚናቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኮሚሽኑ የተቀረፁ አጀንዳዎችን አዳምጠው ግብዓት እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡