በአሜሪካ የምክክር መድረክ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ገቢ ተደረጉ
ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ነሀሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ አጀንዳ ማሰባሰቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ መድረክ የተሰበሰቡ 20 የአጀንዳ ሰነዶችን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ገቢ አድርገዋል፡፡
አጀንዳዎቹ በአስር ቡድኖች፣ በአራት ተቋማት እንዲሁም በስድስት የግለሰቦች ስብስብ የቀረቡ ናቸው፡፡
አጀንዳዎቹን ከሰጡ አካላት መካከል አትሌቶች፣ ምሁራን፣ ግለሰቦች በተናጠልና በቡድን፣ የሚዲያ ሰዎች፣፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ሴቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሲቪክ ማህበራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በ20 ጥራዝ የተሰነዱት አጀንዳዎቹ የገፅ ብዛታቸው 117 ሲሆን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የቀረቡ ናቸው፡፡
በኮሚሽኑ የአሠራር ሥርዓት መሠረት አጀንዳዎቹ ከሌሎች አጀንዳዎች ጋር በኮሚሽኑ ምክር ቤት ተቀርፀው ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡





