በትግራይ ክልል የሚገኙ ፓለቲካ ፓርቲዎች የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገለፁ
ሀምሌ 25/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኮሚሽነሮች ልዑክ በትግራይ ቆይታው በክልሉ ከሚገኙ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።
በተለያዩ መድረኮች በተካሄዱ ውይይቶች ስለ ኮሚሽኑ የእስካሁን የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም በትግራይ ክልል ምክክር በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ በኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ገለፃ ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ኮሚሽነሮች በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን መነጋገር፣ መመካከር እንደሚገባ ገልጸው፤ እንደ አንድ ሀገር ልጆች በመቀራረብ በትግራይም ሆነ እንደ ሀገር የገጠሙንን ችግሮች ለመፍታት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱ እንዲጀመር አስቻይ ሁኔታ በመፍጠርና በንቃት በመሳተፍ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ በመድረኮቹ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የፓርቲ አመራሮቹ ኮሚሽኑ ፈታኝ ሁኔታዎችን በመቋቋም በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለመጀመር ወደ ተግባር መግባቱ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፍጥነት የምክክር ሂደቱ ሊጀመር እንደሚገባው አሳስበው የምክክር ሂደቱ ውጤታማ መሆን ለሚታዩ ችግሮች በዘላቂነት መፈታትና በተለይ በትግራይ የሚታዩ ውጥረቶች ተባብሰው ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ያለውን አውድ የሚያንጸባርቅ የምክክር ሥነ ዘዴ ተቀርጾ ሁሉንም ወገን አካታችና አሳታፊ የሆነ ምክክር እንዲካሄድ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች በስፋት መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ የወሰዳቸውን ግብዓቶች በመጠቀም በክልሉ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር በአጠረ ጊዜ እንዲጀመርና ሁሉንም አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ውይይቱን የመሩት ኮሚሽነሮች ገልጸዋል፡፡





