“በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ ነው” ኮሚሽኑ
ሀምሌ 11/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሠ በወቅታዊ የኮሚሽኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎች በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉበትና ሀሳባቸው የሚደመጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ኮሚሽኑ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎች በምክክር ሂደቱ ቢሳተፉ የሂደቱን አሳታፊነትና አካታችነት ይበልጥ ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳለው የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ በማረሚያ ቤት ያሉ ወገኖች የሚሰጡት የአጀንዳ ግብዓት ካሉበት አውድ አኳያ የራሱ መልክ ስላለው ለምክክር ሂደቱ በእጅጉ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ጋር ታራሚዎች በምክክር ሂደቱ መሳተፍ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጧ፡፡
ከክልል ማረማያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ዕቅድ ስለመያዙም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ሲሳተፉ ቆይተው አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ከተሳትፎ ከታቀቡ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ጥበቡ፤ የፓርቲዎቹ አመራሮች በምክክር አስፈላጊነት እንደሚያምኑ በውይይቱ ወቅት መናገራቸውን አብራርተዋል።
ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ጉዳዮች መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው ኮሚሽኑ እንደሚያምን እንዲሁም አንዳንድ ጉዳዮች ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች ውጭ በመሆናቸው ውጤት ለማምጣት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ አቶ ጥበቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምክክር ሂደቱ የሴቶች ተሳትፎ ትርጉም ያለው እንዲሆን እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር ኮሚሽኑ ሥራዎችን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተም ቃል አቀባዩ መረጃ ሰጥተዋል።
የዚሁ ጥረት አካል የሆነ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር እና ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ወ/ሮ ሲሞኒ ጋር በስትራቴጂያዊ የአጋርነት ዘርፎች ላይ የሀሳብ ልውውጥ መደረጉንም ቃል አቀባዩ አቶ ጥበቡ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኞች ከመግለጫው በመነሳት ጥያቄዎችን ጠይቀው በቃል አቀባዩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።





