በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ በርካታ ባለድርሻ አካላትን (ባለ ደንታዎችን) የማሳተፉ ምክንያት ምንድነው?
ሰኔ 12/2017 ዓ.ም
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ዜጎችን እና በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ባለ ደንታዎችን በማሳተፍ ሂደቱን ውጤታማ እና ምሉዕ ለማድረግ ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የአሰራር ስርዓት መሰረት በወረዳ፣ በክልል፣ በፌዴራል እና በዲያስፖራው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ ቡድኖችን፣ ማህበራትን እንዲሁም ሀገር አቀፍ ተቋማትን በተለያየ ደረጃ እያሳተፈ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡
በእሳካሁኑ ሂደት ኮሚሽኑ በወረዳ እና በክልል/ ከተማ አስተዳደር ደረጃ እንዲሁም በፌዴራል ደረጃ ለሚያከናውነው የምክክር ሂደት ተባባሪ አካላትን ጨምሮ 70 የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት የሂደቱ ቁልፍ ከዋኞች ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል፤ በመስራትም ላይ ይገኛሉ፡፡
ኮሚሽኑ የእነዚህን ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲያበረታታ አካታችነትን እና አሳታፊነትን ለማረጋገጥ ከመሆኑ በተጨማሪ ቁልፍ የስነ ምክክር ንድፈ ሀሳቦችን በመከተል ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ሀሳቦች ይህንን ያብራራሉ፡፡
- የውይይት ተኮር ዲሞክራሲን ለማዳበር፤
ውይይት ተኮር (Deliberative) ዲሞክራሲ የሀገራዊ ምክክር ከተመረኮዘባቸው ንድፈ-ሀሳቦች አንዱ ሲሆን በባህሪው የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያበረታታና የጋራ ውሳኔ ሰጪነት እንዲጎለብት የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ ዓውድ የዜጎች እና የባለድርሻ አካላት ድምፆች የሚደመጡት በአብላጫ ድምፅ ሳይሆን የመከባበር እና የመደማመጥ መርህን በመከተል ሀሳባቸው እንደ አንድ ግብዓት እንዲካተት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የሀገራችን የምክክር ሂደት ውክልናን ከመተግበር ባለፈ ባለድርሻ አካላት እና ዜጎች ሀሳባቸውን እና ስጋታቸውን የሚያሰሙበት(የሚያንጸባርቁበት) እንዲሆን ሂደቱ አበክሮ ይሰራል፡፡
- ማህበራዊ ውልን ለማደስ ብሎም ለማስጠበቅ፤
የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚመሰረትበት ሌላኛው ንድፈ ሀሳብ ሂደቱን ለማህበራዊ ውል ማደሻ ብሎም ማስጠበቂያ ለመጠቀም ነው፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በበቂ ሁኔታ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ባረጋገጠ መጠን እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል እርስ በእርስ ለመስማማት እና ለመግባባት ዕድል ያገኛል፡፡ ይህም ሁሉም ባለ ደንታ ነኝ የሚል አካል ችግሮቹን እና ስጋቶቹን ከሌሎች ጋር በጋራ ተነጋግሮ የጋራ የሚባል ራዕይ እንዲኖረው መንገድ ይፈጥርለታል፡፡ በዚህም አብሮ ለመኖር የሚያስችለውን ማህበራዊ ውል ያድሳል ብሎም ያስጠብቃል፡፡
- የስነ-ምግባር እና የታሪክ ሀላፊነቶችን ለመወጣት፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለቸው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የብዙ ባለድርሻ አከላትን ተሳትፎ ሲያበረታታ ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት ህልውናቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያደርሱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የመወሰን መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ዒላማ በማድረግ ነው፡፡ ይህም ሀገራዊ መግባባት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መከናወን እንዳለበት እንጂ በጥቂት ግለሰቦች ብቻ እንደማይሰራ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!