የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት የሚደነቁ ተግባራትን አከናውኗል- የምክር ቤት አባላት

የካቲት 11/2018 ዓ.ም

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ በአንደኛ አመት አስቸኳይ ጉባኤው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለሁለተኛ ጊዜ ለስምንት ወራት አራዝሟል።

የኮሚሽኑን የስራ አፈፃፀም ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) አራት አመት ሊደፍን ሶስት ቀናት ብቻ የቀሩት ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ 1ሺ 232 ወረዳዎችን በማካለል 93 በመቶ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ምክክር ማካሄዱን አንስተዋል።

አክለውም በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል እንዲሆኑ ጥረት ማድረጉንም ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በተራዘመለት አንድ ዓመት ስራውን ማጠናቀቅ ያልቻለው ትግራይ ክልልን በምክክሩ ሂደት ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት ተግዳሮቶች ስለገጠሙት እንደሆነም አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል ምክክር ለማካሄድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር 17 መድረኮች መከናወናቸውን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ እስካሁን ተሳታፊዎችን መለየትና ክልላዊ የምክክር መድረክ ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል።

የቀጣይ የኮሚሽኑ ዐበይት ተግባራት የትግራይ ክልል ምክክርን ማሳካት፣ የአሰራር ስርዓቶችን ቀርፆ በመዘርጋት ሀገራዊ ጉባዔውን ማካሄድ መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ የታጠቁ አካላትን በምክክሩ ለማሳተፍ አበረታች ስራ መስራቱን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ በቀጣይ በሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሴቶች ተሳትፎ 45 በመቶ እንዲሆን መሰራቱንም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሪፓርቱን ያዳመጡት የምክር ቤቱ አባላት ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጠ ጭምር ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

ይህ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ ሀገራዊ ፕሮጀክት እንዲሳካ ከኮሚሽኑ ጎን መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ ጊዜ የወሰድነው ስራውን በጥንቃቄ ለማከናወን ባደረግነው ጥረት መሆኑን ምክር ቤቱ ይረዳልን ሲሉ ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ ቀጣይ እንቅስቃሴ ላይ የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኮሚሽኑ ቀሪ ስራዎቹን አጠናቆ ምክክሩ ግቡን ይመታ ዘንድ ስምንት ወራት እንዲጨመሩለት ምክር ቤቱን ጠይቋል።

የቀረበውን ውሳኔ የመረመሩት የምክር ቤት አባላት የቀረበውን ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል።