የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ምሁራን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ አበርክቷቸውን ከፍ ማድረግ ይገባቸዋል ተባለ

m4
ምሁራን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ አበርክቷቸውን ከፍ ማድረግ ይገባቸዋል ተባለ
ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ የውይይት መድረኩን ያሰናዳው ምሁራን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ለሂደቱ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ-ሀሳቦችን ለማሰባሰብ ነው፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ጥቂቶች የሚሳተፉበት ሂደት ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ባለቤት የሚሆንበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም ምሁራን ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም ጥናት እና ምርምሮችን እያከናወኑ ሂደቱን ማገዝ እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) የኮሚሽኑን የሶስት ዓመት ዐበይት ክንውኖችና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሀሳብ ያቀረቡት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ምሁራን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ተሳትፎ የማድረጋቸውን አስፈላጊነት በተለያዩ ሳይንሳዊ አመክንዮዎች አስረድተዋል፡፡
ምሁራን በሂደቱ ከመሳተፍ መታቀባቸው በሀገራችን ያሉ ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ የሚፈታ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽነር አምባዬ በማብራሪያቸው የምሁራን በሂደቱ መሳተፍ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በምክክር ሂደቱ ላይ ጥንካሬን እንዲያዳብር እንደሚያደርግ ጠቁመው ሁሉም ሀገራዊ መግባባት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ አሳስበዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታዎችም ኮሚሽኑ በእስከአሁኑ ጉዞው ባከናወናቸው ተግባራት እና ወደ ፊት በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን፣ ጥያቄዎችን እና ምክረ-ሀሳቦችን በማንሳት ውይይት አድርገዋል፡፡