መገናኛ ብዙኃን የሀገራዊ ምክክሩን አውድ መሠረት አድርገው እንዲዘግቡ ተጠየቀ
የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመገናኛ ብዙሀን ተቋማት አመራሮች እና ባለሞያዎች ጋር በቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራዎች እና የመገናኛ ብዙሀን ተሳትፎ ዙሪያ ውይይት አከናውኗል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ፤ ሚዲያዎች የኮሚሽኑን ሥራዎች ለሕዝብ ከማድረስ ረገድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም መገናኛ ብዙኃኑ በቀጣይም ሂደቱን በስፋት እንዲዘግቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የምክክር ዘገባ መርሆችን የሚዳስስ ሳይንሳዊ ትንተና አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ማብራሪያ መሠረትም የሀገራዊ ምክክሩን አጠቃላይ አውድ መሠረት በማድረግ ዘገባ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
መገናኛ ብዙኃን አካታችነትን፣ ወካይነትን፣ ግልጽነትን፣ መረጃን ማዋሃድና ማቀናበርን በሥራዎቻቸው ላይ በማካተት ማኅበረሰቡ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኮሚሽኑ የአራት ዓመታት አፈጻጸም፣ ቀጣይ ዕቅዶች እና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የተከናወኑ የአጋርነት ተግባራት በኮሚሽኑ ባለሞያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከኮሚሽኑ ጋር በቀጣይነት ስለሚያከናውኗቸው ተግባራትም ሀሳቦቻቸውን አንጸባርቀዋል፡፡





