የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ልሂቃን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ

elites and the nd

ልሂቃን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ

ታህሳስ 6/2018 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከዲሞክራሲ ልምምዶች አንዱ እንደመሆኑ የብዙ ከዋኞችን ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ሂደቱ አሳታፊነትን እና አካታችነትን እንደ ቁልፍ መርሆዎቹ በመውሰድ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ሀሳብ እና ተሳትፎ ማረጋገጥ እንዲሚገባው የስነ-ምክክር መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡

ይህንንም መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሕብረተሰቡ በራሱ ችግር ላይ ራሱ ተመካክሮ መፍትሔን ማምጣት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አለው፡፡ በመሆኑም በሂደቱ ላይ ጉልህ ሚናን ሊጫወቱ የሚችሉ አካላት ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ስነ-ዘዴ መሰረት ተሳታፊ እንዲሆኑ መንገዱ ሲመቻች ቆይቷል፡፡

ስነ-ዘዴው ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚያደርጋቸው አካላት መካካል ልሂቃን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ልሂቃን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ እንዴት እንደሚሳተፉ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ጥያቄን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡ በተለምዶው ልሂቃን ተብለው የሚጠሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች በሕብረተሰቡ ዘንድ ተፅዕኖን በመፍጠር በተለያየ ደረጃ ሊገለፅ የሚችል ቦታ የያዙ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በብዙ መደብ ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን ሀገራቱ ሂደቱን ሲያከናውኑ በተለያየ ደረጃ የሚገለፁ ልሂቃንን ማሳተፋቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ልሂቃን መካከል የፖለቲካ ልሂቃን፣ የኢኮኖሚ ልሂቃን፣ የማሕበራዊ ልሂቃን፣ ወታደራዊ ልሂቃን እና የመገናኛ ብዙሃን ልሂቃን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሂደቱ የእነዚህን ልሂቃን ተሳትፎ እና ስብጥር በአግባቡ ጥቅም ላይ ያዋሉ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውጤታማ ከመሆናቸው ባሻገር ለሌሎች ሀገራት ልምድን ትተው አልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ውስጥ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የልሂቃን ተሳትፎ አንዱን እና ዋናውን ቦታ ይዟል፡፡ ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊ የሚሆኑ ወኪሎችን ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ ማሕበራዊ ልሂቃንን በተሳታፊነት ብሎም በተባባሪ አካላትን እንደየአካባቢው ዓውድ ሲያሳትፍ ቆይቷል (የሃይማኖት መሪዎች፣ የማሕበረሰብ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቃዲዎች፣ የጎሳ መሪዎች ወዘተ) ፡፡

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ላይ ጉልህ ሚናን ሊጫወቱ የሚችሉ ከዋኞችም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከወረዳ ጀምሮ ሲከናወን በነበረው እና በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ወኪሎችን በማስወከሉ ሂደት ላይ የንግድ ማህበረሰቡን በመወከል የተለያዩ ተወካዮች መዋቅሮቻቸውን በመጠቀም ሲሳተፉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ባከናወነባቸው 11 ክልሎች እና 2 የከተማ መስተዳደሮች ውስጥ ባላቸው መዋቅር የንግድ ማህበራት ምክር ቤቶችን፣ የአሰሪዎች ማህበራትን እና የሰራተኞች ማህበራትን ተሳታፊ እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህ ከዋኞችም በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ሚና እንዳለቸው ይታመናል፡፡ በመሆኑም በሂደቱ ጎምቱ ሊባሉ የሚችሉ እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በዚህ መዋቅር ውስጥ ተሳታፊዎች መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ልሂቃን ሂደቱ በሚጋብዘው መሰረት በተለያዩ ደረጃዎች ተሳታፊ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ አካታችነት እና አሳታፊነትን ለማስጠበቅም ኮሚሽኑ በክልሎች በሚያከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፖርቲዎችን በማሳተፍ እና በፖለቲካው ምህዳር ላይ ያገባናል የሚሉ ተወካዩችን በመሰብሰብ መልካም ውጤቶችን ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል፡፡

ወታደራዊ ልሂቃንም ሌሎቹ በሂደቱ ሊሳተፉ የሚገባቸው አካላት ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ የቀድሞ ሰራዊት አባላት እና በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን ይህም ወታደራዊ ልሂቃን በሂደቱ የሚኖራቸውን ሚና በመረዳት ነው፡፡ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች በፀጥታው መዋቅር ውስጥ ያሉ ተቋማት ኮሚሽኑ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ሲሰበስብ በንቃት ተሳትፎ ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ለሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳካት የሚዲያ አካላት የጎላ ሚና ቀላል ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትም ሀገራዊ እና ክልላዊ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ከላይ የተጠቀሱት የልሂቃን ስብስቦችን ማሳተፉ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲከናወኑ በቆዩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች በየአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በማሳተፍ በሂደቱ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲጋብዝ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች አንቱታን ያተረፉ እና ተዓማኒነት ያላቸው ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ኮሚሽኑ የምሁራንን ሀሳብ እና ድምፅ ለመስማት እድሉን አመቻችቷል፡፡ በመሆኑም በሁሉም የሀገራችን ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምርት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ መምህራን ስለሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ሀሳቦች በተወካዩቻቸው በኩል እንዲያቀርቡ እና በክልሎች/ ከተማ አስተዳደሮች/ በፌዴራል ደረጃ በተዘጋጁት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ በኮሚሽኑ አሰራር ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በቀጣዮቹ ጊዜያትም የምሁራንን ሀሳብ በተሻለ መልኩ ለመስማት እና የሂደቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኮንሶርቲየም ጋር በመተባባር እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ለሚያሰናዳው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የልሂቃንን ሚናና ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይሻል፡፡ ስለሆነም በዚህ አጋጣሚ በትግራይ ክልል የምትገኙና በተለያየ መዋቅር ውስጥ ያላችሁ ልሂቃን የኮሚሽኑ ተግባራት ለመደገፍ እና በሂደቱ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት እንድታደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽኑ በርካታ የሚባሉ ውይይቶችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ በተከተላቸው የአሰራር ስርዓቶች ውስጥ አልተካተትንም የሚል ቅሬታ ያላቸው አካላት ካሉ ኮሚሽኑ ሀሳባቸውን ለማስተናገድ ሁሌም በሩ ክፍት እንደሆነ ያሳውቃል፡፡