“ለቀሪ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች መሳካት የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው” – ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ(ፕሮፌሰር)
ህዳር 8/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአዳማ ከተማ ከህዳር 5-6/2018 ዓ.ም ተወያይቷል፡፡
ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በዚህ መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት ኮሚሽኑ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በሀገራችን እየተንቀሳቀሱ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መከካል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡
በምክክር ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎችን ለማሳተፍ ኮሚሽኑ በራሱ መንገድ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑትን ሀገራዊ ምርጫ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጣጥሞ መጓዝ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ይህን ለማከናወን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብ ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ የምክክር ምዕራፎች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚናውን እንዲወጣም ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስለ ትግራይ ክልል የምክክር ተሳትፎ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ያሉ ችግሮች ተፈተው ወይም በችግሮቹ መካከል በማለፍ የትግራይ ክልል እንደሌሎች ክልሎች በምክክር ሂደቱ መሳተፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የኮሚሽኑ እምነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡





