ለመመካከር ፈቅዶ የመቀመጥ ጠቀሜታዎች
ሰኔ 6/2017 ዓ.ም
በዓለማችን ላይ የሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰቦች በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ እያለፉ ችግሮቻቸውንም በራሳቸው እየፈቱ አሁን ላሉበት የስልጣኔ ደረጃ ደርሰዋል፡፡
አብዛኛው አፍሪካዊ ማህበረሰብ ግጭቶችን የሚፈታበት መንገድ ተቀራራቢነት ቢኖረውም ሁሉንም ግን አንድ የሚያደርጋቸው አንድ ቁልፍ ድርጊት አለ፤ ለመነጋገር መቀመጥ፡፡ መቀመጥ ለሀገራዊ ምክክር፣ ለግጭት አፈታት እና ለሌሎች የሰላም ግንባታ ሂደቶች ምን ዓይነት በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ለሚለው የሚከተሉት ሀሳቦች ያብራራሉ፡፡

በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ለመነጋገር ፈቅደው ሲቀመጡ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚገኙ በዚህ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ሰዎች ለመነጋገር ሲቀመጡ የመንፈስ መረጋጋት ውስጥ በመሆን ፤ ራሳቸውን በመግዛት እና የማመዛዘን አቅማቸውን በመጠቀም የተረጋጋ ስብዕናቸው ዕውን ይሆናል፡፡ ይህም ለውይይት እና ለምክክር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

ለመመካከር መቀመጥ ራሱን የቻለ የእኩልነት መገለጫ ነው፡፡ ሁሉም አካላት ለንግግር ሲቀመጡ አንዳቸው ከሌላቸው እንደማይበልጡም ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ሀገራዊ ምክክርን በሚመስሉ መድረኮች ላይ ሰዎች ለምክክር ሲቀመጡ ክብ ቅርፅ ሰርተው ሲሆን ይህም የሀይል ሚዛንን ለማመጣጠን ታስቦ ነው፡፡

በሀገራዊ የምክክር ሂደት የሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድነት ለመነጋገር መቀመጥ እና መዘጋጀት ሁሉም አካላት እርስ በእርስ እንዲተማመኑ ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ማለት አንዱ ወገን ሌላኛው ወገን ያጠቃኛል ብሎ ከማሰብ ይልቅ ተቃውሞውን፣ ስጋቱን እና ፍላጎቶቹን ለመናገርና የሌላውን ለማድመጥ ሲፈቅድ መተማመን ይደረጃል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!