ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት መሳካት የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው- ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)
ህዳር 23/2081 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ ዛሬ ህዳር 23/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ካፕታል ሆቴል አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ(ፕሮፌሰር) ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
እስካሁን የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲሳካ ላደረጉትና አሁንም እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ እና አጋርነት ዋና ኮሚሽነሩ ተቋማቱን አመስግነዋል።
በቀጣይም መፍትሔ በማፍለቅ ረገድ ያካበቱትን ልምድና በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸዉን ሰፊ ተቀባይነት በመጠቀም ለምክክሩ ዉጤታማነት ሳይሰለቹ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
የሀይማኖትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የትግራይ ክልል በምክክሩ የመሳተፍ እድሉን እንዲጠቀም ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከመሳተፍ የታቀቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ለማስቻል እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ሀይሎች ያሏቸውን አጀንዳዎች ወደምክክሩ አምጥተው በምክክሩ ሂደቱ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድም የበኩላቸዉን ሚና እንዲወጡ ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በውይይት መድሩኩ ላይ የኮሚሽኑ የእስካሁን የስራ ሂደት፤ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች፣ በሀገራዊ ምክክር የሐይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበራት ሚና የሚሉ መነሻ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።





