ሀገራዊ እና አህጉራዊ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ለሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚሰጡት ትምህርት
ሀምሌ 9/2017 ዓ.ም
አህጉራችን አፍሪካ ባህላዊ እና በማህበረሰቡ የተገነቡ ስርዓቶችን ለእርቅ ፣ ለሰላም ግንባታ እና አብሮነትን ለማስጠበቅ ስትጠቀም ኖራለች፡፡
ከሰሀራ በረሃ በታች ባሉ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሚተገበረውና ኡቡንቱ በመባል የሚታወቀው ስርዓት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ሲሆን ‘I am because you are’ የሚለው ብሒል የዚህን ስርዓት ፍልስፍና ያንፀባርቃል፡፡
ስርዓቱ የተለያዩ ቡድኖች አለመግባባቶቻቸውን በንግግር፣ በዕርቅ፣ እና በይቅርታ በመፍታት ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸውና መስተጋብሮቻቸውን አድሰው አብረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም ያሉ የዕርቅ እና የሽምግልና ስርዓቶች ከዚህ የተለዩ ባይሆኑም የማህበረሰባችንን ወጎች ባገናዘበ መልኩ በዳይና ተበዳይ ችግሮቻቸውን በግልፅ ተነጋግረው እንዲስማሙ ብሎም ሰላም እንዲሰፍን ሲሰሩ ኖረዋል፡፡
ጥያቄው አሁን የገባንበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከእነዚህ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ዕውቀቶች ምን ዓይነት ትምህርት ሊቀስም ይችላል የሚል ነው፡፡
የተወሰኑትን ለመጥቀስ፦
1. የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ግልጽና ሐቀኛ ተሳትፎ፤
2. ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በግልጽ እና በዕውነት ይቅርታ መጠየቅ እንዲሁም ዕንባቸውን ማበስ፤
3. ጉዳት የደረሰባቸው እና ልባቸው የተሰበረ ወገኖች የስነ-ልቦና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ፤
4. በሂደቱ የሃይማኖት መሪዎች የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተገቢውን ሥፍራ መስጠት፤
5. በሰው ልጅ እኩልነት እና ነፃነት የማመን ብሎም አብሮ የመኖር ዕሴትን የማጉላት አስፈላጊነት የሚሉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!





